
ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት እና ዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ.ር) ገልጸዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) በመካካለኛው ምሥራቅ ያለው ጦርነት እና አለመረጋጋት በሀገራችን የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ እና መንግሥት የሚከተላቸውን አቅጣጫዎች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን የሚከታተል፣ እርምጃ የሚወስድ ችና የነዳጅ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎችን የሚለይ ልዩ ክፍል መቋቋሙንም ይፋ አድርገዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ጦርነት እና አለመረጋጋት በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
በጦርነቱ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጦርነቱ በፊት የአንድ በርሜል ነጭ ናፍጣ ዋጋ 80 ዶላር የነበረ ሲኾን አሁን 230 ዶላር መድረሱን ቤንዚንም ከ70 ወደ 150 ዶላር ማሻቀቡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር የነበራት የረጅም ጊዜ የነዳጅ ግብይት ውል በጦርነቱ ምክንያት መስተጓጎሉን እና አቅራቢ ሀገራቱ ምርቱን ማቅረብ እንደማይችሉ ማሳወቃቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም ምክንያት በግዥ ሂደት ላይ የነበረ ከ180 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ አለመቅረቡን ጠቅሰዋል።
በጦርነቱና አለመረጋጋቱ ምክንያትም በነጭ ናፍጣ ላይ የነበረው የቀን አቅርቦት ከ9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር ወደ 4 ነጥብብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዝቅ ማለቱን ጠቁመዋል።
የተለያዩ ሀገራት ያጋጠማቸውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ተከትሎ የተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እቀባዎችን እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው መርሕ ግን ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ችግሩን በጋራ ለመሻገር መኾኑን ጠቅሰዋል።
መንግሥት የተፈጠረውን የአቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ፣ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይገቱ ነዳጅን ከተጓዳኝ ገበያ ስለሚገዛና የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት በሦስት እጥፍ ዋጋ እየገዛ ለማቅረብ መገደዱን አስረድተዋል።
ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም፣ መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለመታደግ በአሁኑ ወቅት በነጭ ናፍጣ ላይ በአንድ ሊትር 95 ብር፣ በቤንዚን ላይ ደግሞ 42 ብር ድጎማ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
መንግሥት እስካሁን 262 ቢሊዮን ብር ገደማ ድጎማ ማድረጉን ገልጸዋል። በየወሩም ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ብር ለድጎማ እየተመደበ መኾኑ ጠቅሰዋል።
ያጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በሀገር እና በዜጎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳያሳድር እና በፍትሐዊነት ለመምራት መንግሥት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚኾን የቅድሚያ አሰጣጥ ውሳኔ ማሳለፉን ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል።
በዚህም መሠረት፦
👉 ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በማደያ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው
👉 ከፍተኛ አምራች እና የኤክስፖርት ድርጅቶች በቀጥታ
👉 ልዩ ትኩረት የሚሹ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች በቀጥታ፣
👉 የገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች
👉 ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮች፣
👉 የከተማና ሀገር አቀፍ የብዙኃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች
👉 እንዲሁም በናፍጣ የሚሰሩ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ የቅድሚያ የነዳጅ አጠቃቀም አሠራር የሚተገበር መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ውጭ የሚደረግ የነዳጅ ስርጭት ተገቢ ባለመሆኑ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት። ይህንን ውሳኔ በአግባቡ ለማስፈጸም በቅንጅት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል መንግሥት የፌደራልና የክልል ተቋማትን ያካተተና ስርጭቱን 24/7 የሚከታተል የሁኔታዎች ልዩ የመከታተያ ክፍል ማቋቋሙን ይፋ አድርገዋል።
ልዩ የመከታተያ ክፍሉ በማዕከል የሚመራ ሲኾን የነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭት እና አጠቃቀምን የሚከታተል፣ ውሳኔዎችን የሚየቀርብና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የሚለይ መኾኑን ተናግረዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው በነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ዙሪያ ሕገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ 658 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ከ720 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተይዞ ለመንግሥት ገቢ ኾኗል ብለዋል።
ከኅብረተሰቡ የሚጠበቁ ተግባራትን ይፋ ያደረጉ ሲኾን በዚህም መሠረት፦
👉 ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀም፣
👉 የታዳሽ ኃይል አማራጮችን የመጠቀም ስልትን መከተል፣
👉 የእግር ጉዞ ባሕልን ማጎልበት
👉 አላስፈላጊ የጉዞ ፕሮግራሞችን መሰረዝና ማቆም
👉 የሕዝብ ትራንስፖርትን መጠቀም
👉 በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ረገድ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
