የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የሚሳካው ተቋማት በአንድነት ሢሠሩ ነው።

6

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የስምምነት ፊርማ ተፈራርሟል።

በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው(ዶ.ር) ስምምነቱ በክልሉ የእውቀት እና የቴክኖሎጅ ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ስትራቴጅካዊ ነው ብለዋል።

በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን ግንኙነት በማጠናክር ወደ ተቀናጀ ሽግግር የሚወስድ መኾኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የሚሳካው የመንግሥት አሥፈጻሚ አካላት እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአንድነት ሢሠሩ እንደኾነም ገልጸዋል።

ክልሉ ካለው የልማት ፍላጎት አንጻርም ቴክኖሎጅን መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ መኾኑን አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዘው ቢሮው እንደገና ከተቋቋመ በኋላ ሰፊ ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በዲጂታል 2025 ሲተገበር የቆየውን እና በዲጂታል 2030 ተጠናክሮ የቀጠለውን የቴክኖሎጅ አጋርነት እና ትብብር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ያለውን የቴክኖሎጅ ዕውቀት እና ሽግግርን ለማሳደግ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለዚህ ስኬታማነትም በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ባለድርሻ በማድረግ በቴክኖሎጅ ሽግግሩ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ ትብብር ማዕቀፉ መሠረታዊ መኾኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የመንግሥት አገልግሎቶች እንዲሳለጡ እና የቴክኖሎጅ መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ በማድረግ የክልሉን ኢኮኖሚ እንዲደግፍ ግብ አስቀምጦ እየሠራ መኾኑን አብራርተዋል።

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) ስምምነቱ በጋራ የምንሠራቸውን ተግባራት ዘላቂነት ባለው መንገድ ለይቶ ለመሥራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በቀጣይም በክልሉ ለሚያስፈልጉ የቴክኖሎጅ ፍላጎቶች በተቀናጀ መልኩ በውጤታማነት ለመግበር በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጡት ማርሸት ግርማዬ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጅ ዘርፍ ለሚሠራቸው ተግባራት የፖሊሲ እና ስትራቴጅክ አቅጣጫዎችን ተከትሎ ለመሥራት እንደሚጠቀሙበት አንስተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጅ ዘርፍ ለሚሠራው የሥራ ዕድል ፈጠራም ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርለት ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአዳዲስ የለውጥ ምዕራፎች የሚከፈቱት በአዳዲስ ችግሮች ወቅት ነው።
Next articleለሰላም ግንባታ ዕውነትን፣ ሰላምን እና ፍትሕን ማስተማር ከሚዲያዎች ይጠበቃል።