
ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጦርነት ምክንያት የሚከሰቱ የወደቦች እና መተላለፊያዎች መዘጋት እና ማዕቀብ በዓለም ታሪክ ሀገራትን ለኢኮኖሚ ችግር ሲዳርጉ ይስተዋላል።
እነዚህን ቀውሶች ለመሻገር የተወሰዱ እርምጃዎች ታዲያ እጅግ አስገራሚ እና የሰው ልጅን የፈጠራ አቅም ያሳዩ ናቸው።
ከበርሊን ሰማይ እስከ ደቡብ አፍሪካ የከሰል ፈሳሽ የተፈጥሮ ነዳጅ የተስተዋሉት ክስተቶች ሀገራት ህልውናቸውን ለማስቀጠል ምን ያህል ርቀት እንደሚጓዙ የታየበት ነው።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ሶቪየት ኅብረት ወደ በርሊን የሚወስዱ የየብስ እና የውኃ መተላለፊያዎችን በሙሉ ዘግታ ነበር። ያኔ ምዕራባውያን ሀገራትም በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ “የአየር ላይ ድልድይ” በመዘርጋት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከረሃብ መታደግ ችለዋል።
ይህም የትራንስፖርት ቴክኖሎጂን ለሰብዓዊ እርዳታ የመጠቀም ጥበብን ለዓለም አስተምሯል።
በሌላ በኩል በ1960ዎቹ አጋማሽ የስዊዝ ቦይ ለስምንት ዓመታት ያህል በተዘጋበት ወቅት የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ አዲስ አቅጣጫ ለመፈለግ ተገዶ ነበር። ይህም “የሱፐር ታንከር” ግዙፍ መርከቦች ግንባታ ነው።
መርከቦች በአፍሪካ ዙሪያ ረጅም መንገድ ስለሚጓዙ የወጭውን መናር ለመቋቋም ሲባል በስፋት መመረት የጀመሩበት አጋጣሚ ነበር። ይህ ክስተት ታዲያ በባሕር ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣቱ ይታመናል።
የወደብ መዘጋት እና ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች በአፍሪካ ላይም የኢኮኖሚ ጫና ሲፈጥሩ ኖረዋል። ይህንን በፈጠራ በመቋቋም ረገድ የደቡብ አፍሪካን ታሪክ በቀዳሚነት አስፍሯታል።
ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ዘመን የተጣለባትን የነዳጅ ማዕቀብ የተፈጥሮ ሃብቷን በመጠቀም መክታለች። ከሰልን ወደ ፈሳሽ ነዳጅ የሚቀይር ግዙፍ ፋብሪካ በመገንባት የዓለምን ማዕቀብ በሀገር በቀል ቴክኖሎጂ የተቋቋመችበት መንገድ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያም ከቀይ ባሕር የወደብ ባለቤትነት በኢ-ፍትሐዊ መንገድ ስትገፋ የገቢ እና ወጭ ንግዷን በአጭር ጊዜ ወደ ጅቡቲ በማዞር በኋላም ዘመናዊ የባቡር መስመር በመዘርጋት ወደብ አልባነትን የመቋቋም ሥልታዊ እርምጃ ወስዳለች። የገጠማትን ድንገተኛ የንግድ መስተጓጎል በጥበብ ማለፏ የቅርብ ዓመታት ትውስታ ነው።
በዓለም አቀፍ ጦርነቶች እና ማዕቀቦች የተነሳ የወደቦች እና የንግድ መስመሮች መዘጋት ሀገራትን ለኢኮኖሚያዊ ጫና እንደሚዳርጉ እሙን ነው። ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱት ብርቱ እርምጃዎች ግን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩ፤ አማራጭ የንግድ መስመሮች እንዲዘረጉ እና የሀገራት የውስጥ አቅም እንዲጠናከር ምክንያት ኾነዋል።
አሁንም ዓለም ጦርነት ከሚወልደው ችግር አልተላቀቀችም። የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት የሆርሙዝ ወሽመጥ እና ሌሎች መተላለፊያዎች ላይ ችግር ፈጥሯል። በዚህም ሀገራት ለኢኮኖሚ ቀውስ እየተዳረጉ እንደኾነ እየተነገረ ነው። ይህን ችግር ለመቋቋምም የተለያዩ ጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሔዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
የቢዝነስ ስትራቴጅ እና ኢንቨስትመንት አማካሪው ጌታቸው መላኩ (ዶ.ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት መቆራረጥ አሁን ብቻ የተከሰተ አይደለም ብለዋል። እ.አ.አ በ1973 እና በ1979 የደቡብ አሜሪካ ሀገራት አጋጥሟቸው የነበረውን ከፍተኛ የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፉ የኢነርጅ ኤጀንሲ የተቋቋመውም በ1973 የተከሰተውን የነዳጅ ቀውስ ተከትሎ እንደኾነ አንስተዋል። ድርጅቱ እንደዚህ ዓይነት የነዳጅ መቆራረጥ ሲከሰት መፍትሔ ለማፈላለግ የተቋቋመ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዶክተር ጌታቸው የነዳጅ ችግር አዲስ ነገር አይደለም፤ በየጊዜው ሊከሰት የሚችል ነው ብለዋል። የኢነርጅ ፖሊሲ በመቅረጽ የሚያስፈልገውን ኢነርጅ፣ የሚገኝበትን ቦታ እና እንዴት እንደሚገኝ በደንብ መተንተን እና በዚያ መመራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
አሁን የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ እንደ ኬንያ እና ሴሪላንካ ያሉ ሀገራት የመሠረታዊ ምርቶች አዋጅ አውጥተው ተግባራዊ እያደረጉ መኾናቸውንም አንስተዋል። ስትራቴጅክ ነዳጅ መጠባበቂያ መጠቀም፤ አስገዳጅ የነዳጅ ቁጠባ መመሪያዎችን ማውጣት፤ የተለያዩ የነዳጅ አማራጮችን የማፈላለግ ሥራ በተለያዩ ሀገራት ተግባራዊ እየተደረገ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያም ችግሩ በማንኛውም ጊዜ ሊገጥም እንደሚችል አስባ እንደ ሌሎች ሀገራት ሁሉ የነዳጅ እና መሰል መሠረታዊ ምርቶች ፖሊሲ እና ስትራቴጅ ማዘጋጀት፤ የአስፈላጊ ግብዓቶች ሕግ አውጥቶ በሕግ እና በሥርዓት መምራት እንደሚያስፈልጋት አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ያላት ሀገር ናት። በመኾኑም የኤሌክትሪክ ኃይልን በመጠቀም እና በዚሁ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን በማብዛት ቀጣይ ጉዞዋን መቀየር ትችላለች። አዳዲስ ችግሮችን ለመልካም የለውጥ ምዕራፎች ማስጀመሪያ አድርጎ በመጠቀም ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት እና የራስን ታዳሽ ኃይል አጠቃቀም ለማጎልበት ጊዜው አሁን ነው።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
