ፈተናን ወደ ዕድል የቀየረ የዲፕሎማሲ ከፍታ።

10

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባጋራው መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ስምንት ዓመታት የተከተለው ንቁና ስልታዊ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የሀገራችንን የውጭ ግንኙነት ለዘመናት በተዛባ መልኩ ይዞት ከነበረው ከያዛት “በጠላቶች የመከበብ እይታ” በማላቀቅ ለላቀ ዓለም አቀፋዊ ከፍታ የሚመጥን መሠረት ጥሏል ብሏል።

የለውጡ መንግሥት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ዋነኛ መለኪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ነው። ሀገራችን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የራሷን የሉዓላዊነት እና የልማት ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት መርህን ስትከተል ቆይታለች ነው ያለው።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙንን ዓለም አቀፍ ጫናዎች በብቃት በመቋቋም እና የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን በማጠናከር እንደ ብሪክስ አባልነት ያሉ የሀገራዊ ክብራችን ማሳያ የኾኑ ስኬቶችን አስመዝግበናል። ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት እና የውሳኔ ሰጪነት ዐቅም በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለው መርሕ ከቃላት ባለፈ በተግባራዊ ዲፕሎማሲ በመተርጎሙ ቀጣናዊ ግንኙነታችን ከጥርጣሬ አጥር ወጥቶ ወደ ጽኑ ስልታዊ አጋርነት ተሸጋግሯል። ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የትስስር ማዕከል በመኾን በታዳሽ ኃይል ፣ በመንገድ፣ በመጠጥ ቅኃ እና በባቡር መሠረተ ልማቶች የቀጣናውን ሀገራት ዕጣ ፈንታ ከራሷ ጋር አስተሳስራለች። ይህ የጋራ ዕድገት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ምሰሶ ብቻ ሳይኾን፣ የማይበገርና መሪ ቀጣናዊ ኃይል እንድትኾን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል ብሏል።

“ዜጋ ተኮር” የዲፕሎማሲ አቅጣጫችን የመንግሥታችን ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ጽኑ ቁርጠኝነት መገለጫ ነው። ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ በሕጋዊ መንገድ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ይህ ሳይኾን ቀርቶ ሰብዓዊ መብታቸው የማይጠበቅበት ሁኔታ ተፈጥሮ ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን ወደ እናት ሀገራቸው ለመመለስ የተከናወኑ ተግባራት መንግሥት ለሕዝቡ ያለውን አለኝታነት ያሳዩና በዜጎች ዘንድ የላቀ ብሔራዊ ኩራት እና መተማመንን የፈጠሩ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው።

በዓለም ዲፕሎማሲያዊ መድረኮች ተፅዕኖዋ እየጎላ እና ጥንካሬዋ እየጎለበተ የመጣው ሀገራችን አሁንም የፓን አፍሪካኒዝም ማማና የፅናት ተምሳሌት መኾኗን ለዓለም በድጋሜ ያረጋገጠ የታሪክ ምዕራፍ ተገኝታለች።
ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ስልታዊ የዲፕሎማሲ ድሎች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ከፍታ አሸጋግረውታል።

ዛሬ ሀገራችን በውጭ ግንኙነቷ የምትታወቀው የቀጣናዊ አጀንዳዎች ምንጭና የመፍትሔ አካል በመኾን ነው። ይህ አዲስ ገጽታችን እና እየተገነባ ያለው ብሔራዊ ኩራት ለሚገጥሙን ተግዳሮቶች እንዳንበረከክ አቅም እና የልማት ጉልበት ኾኖልናል።

በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በሳል፣ በስትራቴጂ የሚመራ እና ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያነጣጣረ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ሥራችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዜጎች በሁሉም መስክ የሃገራቸው አምባሳደር በመኾን የድርሻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል ብሏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥፋት ጉዞን ለመግታት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሃይማኖት መሪዎች ሚና ከፍ ያለ ነው።
Next articleአዳዲስ የለውጥ ምዕራፎች የሚከፈቱት በአዳዲስ ችግሮች ወቅት ነው።