
ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “በመደመር መንግሥት ዕይታ የሃይማኖት መሪዎች ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ከፕሮቴስታንት እና ከካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች ጋር በወቅታዊ እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ምክክር አካሂዷል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የሃይማኖት ተቋማት እና መሪዎች ዋነኛ አስተምህሮ ስለ ሰላም፣ ስለ ሀገር እና ስለ ሕዝብ አንድነት መኾኑን ጠቅሰዋል። ፍቅር እና አብሮነት እንዲሰፍን መሪዎቹ በከፍተኛ ትጋት መሥራት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
የመደመር መንግሥት የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የሰላም እጦት እና ቀውስ በመነጋገር እና በመደማመጥ ወደ መልካም መለወጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የጥፋት ጉዞን ለመግታት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሃይማኖት መሪዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
የከተማዋን የልማት እና የውበት ሥራዎች ለማስቀጠል የጸጥታው ሁኔታ አስተማማኝ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል። በተለይም የጥፋት ተልዕኮን አንግበው የሚንቀሳቀሱ አካላትን በጋራ በመከላከል ለቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊት ከተማን ለማስተላለፍ ሁሉም በቅንጅት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
የሃይማኖት አባቶችም ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት የሰላም እጦት እንድትወጣ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ደሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቲዎስ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሃይማኖት መሪዎች ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ሰላም ከግለሰብ ተነስቶ ወደ ማኅበረሰብ እና ሀገር የሚሸጋገር በመኾኑ እያንዳንዱ ግለሰብ ከራሱ እና ከጎረቤቱ ጋር በሰላም የመኖር እና የእርቅ ባሕልን ሊያዳብር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት የባሕር ዳር ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት
ዋና ጸሐፊ መጋቢ ልንገረው ወርቁ በመንግሥት እና በሃይማኖት ተቋማት መካከል የተጀመረው የምክክር መድረክ ለሀገር ሰላም እና አንድነት መጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ሰላም ከእያንዳንዱ ግለሰብ የሚጠበቅ እና “እኔ እንዲደረግልኝ የምፈልገውን መልካም ነገር ለሌላውም ማድረግ” ከሚለው እሴት የሚመነጭ መኾኑን አስገንዝበዋል።
መንግሥት ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
