“ሕጋዊ እና የጸና መንግሥት የሚረጋገጠው በምርጫ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

13
ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የመራጮች ምዝገባ አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከየካቲት 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ እያካሄደ ነው። ባለፉት ሳምንታትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የመራጮች ምዝገባን አካሂደዋል። ምዝገባው አሁንም መካሄዱን ቀጥሏል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይም የመራጮች ምዝገባ በማካሄድ የምርጫ ካርድ ወስደዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል። እርሳቸውም የመራጮች ምዝገባ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል። መራጩ ሕዝብ የሚፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ማውጣት አለበት ነው ያሉት።
መንግሥት ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ እየሠራ ነው ብለዋል። ማንኛውም ሥልጣን መያዝ ያለበት አካል ሕጋዊ በኾነ መንገድ በምርጫ መኾን አለበት፤ በኃይል የሚደረግ ሥልጣን የጸና አይኾንም፤ ተቀባይነትም የለውም ነው ያሉት።
ሥልጣንን በኃይል የመያዝ ልምምድ ሀገርን እንዳልጠቀመ ያለፉት ታሪኮች አስተማሪ እንደኾኑም አስታውሰዋል። ለኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገው የጸና ሕጋዊ መንግሥት ነው፤ ሕጋዊ እና የጸና መንግሥት የሚረጋገጠው ደግሞ በምርጫ ነው ብለዋል።
ለመምረጥ ዕድሜው የደረሰ እና በሕግ ክልከላ የሌለበት ሁሉ እንዲመርጥም ጥሪ አቅርበዋል። መንግሥት መጽናት ያለበት በምርጫ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ሕዝቡ አስቦ እና አሰናስሎ ለመምረጥ መዘጋጀት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል። ሕጋዊ ያልኾኑ አካሄዶችንም መታገል እንደሚገባው አሳስበዋል።
ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሐምሌ አምስት የመላው አማራ የድል ቀን መኾኑን የሚያመላክት አደባባ በወልቃይት ተገንብቶ ተመረቀ።