
ሁመራ፡ መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ራሱን ሕወሓት እያለ የሚጠራው ቡድን የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ወሰን እና ማንነት ትግል ግንባር ቀደም አንቀሳቃሽ ናቸው ብሎ ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ለማፈን ከሞከራቸው ግለሰቦች መካከል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ይገኙበታል።
በወቅቱ በጎንደር ሕዝብ እልህ አስጨራሽ ትግል ራሱን ሕወሓት እያለ የሚጠራው ቡድን ኮሎኔል ደመቀን ማፈን ሳይችል ቀርቶ በዚያውም የሀገራዊው ለውጥ ትግል ተቀጣጠለ።
በጊዜ ሂደት ሀገራዊው ለውጡ በመጣ ማግስት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የታገለለትን ነጻነት ተቀዳጅቷል።
በመኾኑም ሐምሌ አምስት የተቀጣጠለውን የአማራ ትግል የሚያሳይ አደባባይ ተገንብቶ ተመርቋል።
በዞኑ ዋና መቀመጫ ሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳዳር ላይ ተገንብቶ ለምረቃ በበቃው ሐምሌ አምስት በተሰኘው አደባባይ ላይ የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በምርቃው ላይ ተገኝተው “ሐምሌ አምስት የመላው አማራ ሕዝብ የድል ቀን” መኾኑን ገልጸዋል።
ኮሎኔል ደመቀ ዛሬ ሕዝቡ ላገኘው ነጻነት ውድ ዋጋ የከፈሉ ወንድሞች እልፍ መኾናቸውን ገልጸዋል። “ለከፈሉት ዋጋም ስንዘክራቸው እንኖራለን” ነው ያሉት።
ሐምሌ አምሰት ሁል ጊዜ ሊዘከር የሚገባው የነጻነት ቀን ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ወጣቶች ይሄንን የነጻነት አደራ መረክብ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
