የጋራ ምክርቤቱ ለምርጫው ስኬታማነት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው።

8
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የድርሻውን እየተወጣ መኾኑን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታውቋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጋራ ምክር ቤቱ ሠብሣቢ ተስፋሁን ዓለምነህ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የጋራ ምክርቤቱ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በምርጫ ጉዳይ የጋራ አቋም ተወስዶ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
አቶ ተስፋሁን በምርጫ ሂደት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታትም ራሱን የቻለ ኮሚቴ ተዋቅሮ ክትትል በማድረግ እየተፈታ መቀጠሉንም አንስተዋል።
ከምርጫ ውጭ የሚደረገው አካሄድ ሁሉ አጥፊ በመኾኑ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ምርጫ በሕግ እና በሥርዓት መመራት ይኖርበታል ነው ያሉት። ለዚህም የምርጫ ቦርድን እና የሕግ ማዕቀፎችን አክብሮ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ በተለያየ ጊዜ በመገናኘት የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት፣ ሕዝቡ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መኾኑን በማስገንዘብ፣ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲኾን ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
የአንድ ሰው ድምጽ ዋጋ መኖሩን በመገንዘብ ሕዝቡ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል። መራጩ ሕዝብም በምክንያት ላይ ተመሥርቶ እንዲመርጥ፣ ፓርቲዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንዲችሉ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለዚህም ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን እና ከሚዲያዎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። የምርጫ ክርክሮች መጀመራቸውንም አንስተዋል።
ሚዲያዎችም በምርጫ ሂደት ፓርቲዎችን እና ሕዝብን የሚያገናኙ ናቸው ያሉት አቶ ተስፋሁን አሚኮም በግልጽ መስፈርቶች የፓርቲዎችን ድልድል ለጋራ ምክርቤቱ ማሳወቁን ጠቁመዋል። በዚህም ምሳሌ የሚኾን እና የሚበረታታ ተቋም ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየእናቶች እምባ የሚታበሰው በፍቅርና በመቻቻል ነው!
Next article“የመራጮች ምዝገባ የሚጠናቀቅበትን ቀን አልተቀየረም” ምርጫ ቦርድ