ሀገር የምታተርፈው ከሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ነው።

7

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ተስፋሁን አለምነህ የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ምርጫ ዜጎች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡበት መሳሪያ ነው።

የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ እንደኾነና ይህም የሚረጋገጠው በምርጫ እንደኾነ ጠቁመዋል። ሕዝብ የፈለገውን ወደ ሥልጣን የሚያወጣበት እና ከሥልጣን የሚያወርድበት መንገድ ስለመኾኑም አብራርተዋል።

ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ እንዲሸጋገር እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሕዝብ ድምጽ ተመርጦ ቅቡልነት ያገኘ መንግሥት መኖር ወሳኝ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

ዜጎች በድምጻቸው የሚመርጡት እና ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለዘላቂ ሰላም መደላድልን ይፈጥራል ነው ያሉት።

ፍትሐዊ፣ ተዓማኒ እና ሰላማዊ በኾነ ምርጫ የሚመጣ መንግሥታዊ ሥርዓት ዘላቂ ሰላምንም ይዞ ይመጣል ብለዋል። በሰላም እና በምርጫ ጉዳይ የጋራ ምክር ቤቱ ወጥ አቋም ወስዶ እየሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል።

በዚህም ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ችግሮች ሲፈጠሩም በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

አቶ ተስፋሁን የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን በሠለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ የምንፈታበት አውድ ለመፍጠር ምክር ቤቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

በተለይም ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ወቅት የጋራ ምክር ቤቱ ትልቅ የፖለቲካ አቋም ወስዶ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ እንዲፈቱ ቁርጠኛ ኾኖ እየሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሀገርን በማሥቀደም መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

እኔ ብቻ አውቅልሀለሁ የሚለው አስተሳሰብ ተገቢ እንዳልኾነም አብራርተዋል። ምርጫ አያስፈልግም የሚለውን ኋላቀር አስተሳሰብ ታግሎ በማሸነፍ ቅቡልነት ያለው ምርጫ እንዲኖር ችግሮችን ተጋፍጦ ማለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በትጥቅ ትግል የሚመጣ ዴሞክራሲ የለም ያሉት አቶ ተስፋሁን ሀገር የምታተርፈው ከሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መኾኑንም አስገንዝበዋል።

ከሰላም አማራጭ ውጭ የሚካሄዱ የኃይል እንቅስቃሴዎች አውዳሚ ናቸው ብለዋል። ሀሳብ አለኝ የሚል ሁሉ ሀሳቡን ይዞ ለሕዝብ በመቅረብ የመምረጥ ዕድሉን ለሕዝብ መስጠት እንደሚገባ ነው ያብራሩት።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጦርነት ለማንም አይበጅም” ፍቅሩ ሙሉዬ
Next articleየእናቶች እምባ የሚታበሰው በፍቅርና በመቻቻል ነው!