‎በገና እና ዐቢይ ፆም

4
‎‎ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ በገና ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚቀርብበት፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውል መሣሪያ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በገናን ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ይዛው እንደዘለቀች እና ሃይማኖታዊ ምስጢራትን እንደያዘም ይነገራል።
‎በዐቢይ ፆም ወቅት የበገና መዝሙር በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ይዘወተራል። በዚህ የፆም ወቅት በአብያተ ክርስቲያናት የበገና መዝሙር መስማት የተለመደ ነው።
ለመኾኑ በገና እና ዐቢይ ጾም ያላቸው ትስስር ምንድን ነው?
‎በባሕር ዳር ከተማ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የበገና ማሠልጠኛ ተቋም ባለቤት እና መምህር ሊቀመዘምራን ጌታቸው ብርሃኑ በገና ማለት መዝሙር ማለት ነው ይላሉ።
መዝሙር የግዕዝ ቃል ሲኾን ዘመረ ከሚለው ግስ የመጣ ነው፡፡ በገና ደግሞ የአማርኛው ትርጉሙ ነው ብለዋል፡፡ በገና ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ እግዚአብሔርን ለማመስገን ጥቅም ላይ የሚውል መሣሪያ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
‎እንደ መምህሩ ገለጻ በአሁኑ ወቅት በብዛት አገልግሎት ላይ የሚውለው አሥር አውታሮች ያሉት በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጽ እንዚራ ተብሎ የሚጠራው ነው ብለዋል።
‎በሌላ በኩል በገና የሚባለው ጥልብ ቃና ተብሎ የሚጠራ ሲኾን 150 አውታሮች ያሉት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም በገና በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ውስጥ ያለውን ጥልቅ ምስጢር፣ ረቂቅ ባሕሪ የሚያሳይ እና አሁንም ድረስ ጥቅም ላይ እንደሚውል ነው የተናገሩት። እያንዳንዱ የበገና ክፍሎችም የተለያዩ ሃይማኖታዊ ትርጓሜ አላቸው ብለዋል፡፡
‎በገና እና ዐቢይ ጾም ያላቸውን ትስስር ሲገልጹ ምስጋና ከዐቢይ ፆም ጋር ብቻ አይደለም የሚገናኘው ነው ያሉት፡፡ 365ቱም ቀናት የምስጋና ናቸው ያሉት መምህሩ በሰማይ ያሉ መላዕክትም በበገና ሁልጊዜ ያመሰግናሉ ነው ያሉት።
ይህ ምስጋና እንደማይቋረጥ ሁሉ በገናም ዐቢይ ፆምን ብቻ ተጠብቆ የሚደረደር አይደለም ይላሉ። በዐቢይ ፆም በብዛት ይደረደር ካልኾነ በስተቀር በገና የሁልጊዜ የማመስገኛ መሣሪያ ነው ብለዋል፡፡
‎በገናን ለመደርደር በቅድሚያ ትምህርቱን በሚገባ መማር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ በገና ሲደረደር ንጽሕናን የሚፈልግ በመኾኑ ንስሀ ገብተው በቅድስና ኾኖ መደርደር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ውጤቶች ተገኝተዋል።
Next articleፍቅሩ ሙልዬ የሰላም አማራጭን ተቀበለ።