
ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት፣ ወደ ሀገር ማስገባት፣ መሸጥ እና መጠቀምን በተመለከተ የሚደነግግ አዋጅ 1383/2017 ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው።
አዋጁን መሠረት በማድረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደርም ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም ከዛሬ ጀምሮ የተከለከለ መኾኑን አስታውቋል።
በከተማ አሥተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳት እና ውበት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የአካባቢ ጥበቃ ቡድን መሪ አበቡ ወልደሚካኤል እንደገለጹት ቀደም ብሎ ክልከላው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየቱን አንስተዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ በከተማዋ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ሲጠቀም ወይም ሲያቀርብ የተገኘን አካል በአዋጁ በተደነገገው መሠረት ተጠያቂ ለማድረግ መወሰኑን ለአሚኮ ተናግረዋል።
የፕላስቲክ ምርት ለረጅም ጊዜ የማይበሰብስ በመኾኑ በብዝኀ ሕይወት፣ በሰው እና በእንስሳት ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያመጣ ተናግረዋል። በተለይም በከተማ ካሉት የደረቅ ቆሻሻ ምጣኔ የፕላስቲክ ውጤቶች ከፍተኛውን መጠን እንደሚይዙ ጠቁመዋል።
ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ውሳኔም ከተማዋን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመላክተዋል። ማኅበረሰቡ ጉዳቱን ተገንዝቦ ከፕላስቲክ ከረጢት ይልቅ በቀላሉ የሚበሰብሱ ምርቶችን እንዲጠቀም ባለሙያዋ መክረዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
