ኢትዮጵያ በ11ኛው የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች።

3
ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተሳተፉበት 11ኛው የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓን በቤንሉክስ ሀገራት እና በአውሮፓ ኅብረት ተቋማት የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ገልጸዋል።
11ኛው የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ “የተለወጠ እና የታደሰ የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት ተግዳሮት ለበዛባት ዓለም” በሚል መሪ መልዕክት መጋቢት 19/2018 ዓ.ም እና መጋቢት 20/ 2018 ዓ.ም በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ከተማ ተካሂዷል።
በጉባኤው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ድርጅቱ ተለዋዋጭ በኾነው የዓለም የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ውስጥ የአባል ሀገራቱን ጥቅም የሚያስከብር ጠንካራ ድርጅት ኾኖ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ውይይቱን የተከታተሉት በቤንሉክስ ሀገራት እና በአውሮፓ ኅብረት ተቋማት የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመድረኩ የድርጅቱን አስፊላጊነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያሳድጉ ገንቢ ሀሳቦችን ማካፈላቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባለ ብዙ ወገን ግንኙነትን የመደገፍ የቆየ እሴት እና መርህ ያላት ሀገር ናት ብለዋል።
የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅትን ከመሠረቱ ጥቂት ሀገራት አንዷ መኾኗን ጠቁመዋል። ድርጅቱ እንዲጠናከርም የገንዘብ መዋጮዋን በአግባቡ ከመክፈል ጀምሮ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ማንኛውም ሀገር ብቻውን ሊሠራ የሚችለው ነገር የለም ያሉት አምባሳደር እሸቴ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ያላት ተሳትፎ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በእጅጉ እንደሚያግዛትም ተናግረዋል፡፡
ኢዜአ እንደዘገበው እነዚህን ዕድሎች በአግባቡ ለመጠቀም ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት ወጣቶቻቸውን በብዙ መልኩ ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት እ.አ.አ በ1975 በጆርጅታውን ጉውያና የተመሠረተ ሲኾን በአሁኑ ወቅት 79 አባል ሀገራት አሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአካታች ፖለቲካዊ ለውጦች ለጽኑ ሀገራዊ መሠረት
Next articleለጥንቃቄም ለመረጃም፦