አካታች ፖለቲካዊ ለውጦች ለጽኑ ሀገራዊ መሠረት

7
ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌድሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባጋራው መረጃ የኢፌዴሪ መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራችንን ከነበረችበት ስር የሰደደ ፖለቲካዊ ቀውስ አውጥቶ ወደ ተሟላ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የነደፋቸውን ስልታዊ ግቦች በላቀ ጽናት እና ስኬት ወደ ተግባር ቀይሯል ብሏል።
የዚህ ታሪካዊ ሽግግር ዋነኛ ስኬት ለዘመናት ኢትዮጵያን ሲንድ የነበረውን “የመሐል እና የዳር” አግላይ ፖለቲካዊ ትርክት በመስበር እያንዳንዱ ዜጋና እያንዳንዱ አካባቢ የሥልጣን እና የሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚ የሚኾንበትን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገንባቱ ነው። ይህ ለውጥ ኢትዮጵያ የጥቂቶች ሳይኾን የሁላችንም የጋራ ቤት መኾኗን በተግባር ያረጋገጠ መሠረታዊ ድል ነው።
ለዘላቂ ሰላም እና ለሀገራዊ ሕልውና መረጋገጥ በትውልዶች መካከል ድልድይ የሚኾን የወል ትርክት ግንባታ ላይ የተመዘገቡት ድሎች የለውጡ መንግሥት ታላቅ ፖለቲካዊ ስኬቶች ናቸው። ሀገራችንን ለዘመናት በቅራኔ ውስጥ ዘፍቀው የቆዩ አግላይ ትርክቶች እንዲከስሙ በማድረግ፣ በምትካቸው የሁላችንንም ታሪክ እና አሻራ የሚዘክሩ የጋራ ትርክቶች በተግባር እንዲጎለብቱ ተደርጓል።
በዚህም የታሪክ እና የማንነት መገለጫ የኾኑት የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ በገበታ ለሸገር፣ ለሀገር እና ለትውልድ መርሐ ግብር የተገነቡ ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻዎች የጋራ ሀገራዊ ኩራታችንን ከፍ አድርገውታል።
ብዝኃነትን በውበትነት በመቀበል በብሔራዊ ምክክር መድረክ የቀጠለው ትናንትን የማከም ጉዞም ትናንት በጥርጣሬ እና በክፍፍል ይናጥ የነበረውን ሀገራዊ ትርክት ቀስበቀስ በተግባር ወደ ተረጋገጠ ወንድማማችነትና የጋራ ብልጽግና እየመራው ይገኛል።
የሀገረ መንግሥት ግንባታው ምሰሶ የኾኑትን ተቋማት የመገንባትና የማደራጀት ሥራ በልዩ ቁርጠኝነት ተከናውኗል። በተለይም የፀጥታ፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ተቋማት ለሕዝብና ለሕግ ብቻ ተገዥ እንዲሆኑ የተደረገው ሪፎርም ስር-ነቀል ለውጥ አምጥቷል።
በዚህም መሠረት እንደ ምርጫ ቦርድና ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት በገለልተኛ አመራር እንዲዋቀሩ መደረጉ፣ የመከላከያና የደኅንነት ተቋማት ከአገራዊ ተልእኮ ውጭ ከማንኛውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲጸዱ መደረጋቸውና የፍትሕ ሥርዓቱ በነጻነት እንዲሠራ የተዘረጋው አሠራር የተቋማዊ ሪፎርማችን ሕያው ማሳያዎች ናቸው።
ይህ ስር-ነቀል የፖለቲካ ለውጥ በውስጥ መረጋጋትና በአገራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ኢትዮጵያ የነበሩባትን የህልውና ሥጋቶች በጽናት እንድትወጣ አስችሏታል።
ሉዓላዊነታችንን በፖለቲካዊ ብስለትና በአመራር ጥንካሬ የማስከበር አቅማችን መጎልበቱ፣ የመንግሥትን የፖሊሲ ማስፈጸም ብቃት ከማሳየቱም በላይ አገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ምዕራፍ አሸጋግሯታል።
እነዚህ የፖለቲካ ድሎች በውስጥ የታየው አንጻራዊ የሰላም መስፈን፣ የፖለቲካ ምሕዳሩ መስፋትና የተቋማት መጠናከር ቀጥተኛ ውጤቶች በመሆናቸው አገራችን ለምታደርገው የብልጽግና ጉዞ መሰረት እየጣሉ ይገኛል።
በአጠቃላይ እነዚህ የፖለቲካ ትልሞችና የተጨበጡ ፍሬዎች ኢትዮጵያን ወደ አዲስና የተሻለ የዴሞክራሲ ልምምድ አሸጋግረዋታል። የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ማደግ፣ የመንግሥት ተቀባይነት በሕዝብ ዘንድ ጎልቶ መታየትና የሪፎርም ሥራዎች ስኬታማነት ለብልጽግና ጉዟችን አስተማማኝ ዋስትናዎች እየሆኑ መጥተዋል።
መንግሥት ይህንኑ የዴሞክራሲና የብልጽግና ጎዳና አጠናክሮ በመቀጠል፣ ለትውልድ የምትመች፣ የበለጸገችና ሉዓላዊነቷ የተከበረች ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነቱን በላቀ ቁርጠኝነት መወጣቱን ይቀጥላል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለጥንቃቄ፦ ለእጅ ስልክዎ (ሞባይል) ማድረግ ያለብዎት ጥንቃቄ፦
Next articleኢትዮጵያ በ11ኛው የአፍሪካ፣ ካርቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች።