
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል፣ ኪነ ጥበብ እና ዝክረ ታሪክ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ገብረማርያም ይርጋ በደቡብ ኮሪያ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የባሕል እና የኪነ ጥበብ ሙያተኞች ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ኾነው ተሹመዋል።
የተሰጣቸውን ኀላፊነት በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ገብረ ማርያም ይርጋ መሥሪያ ቤቱ በዓለም ዓቀፍ የባሕል፣ የኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ልማት ሥራዎችን የሚሠራ ተቋም መኾኑን ጠቁመዋል። በተቋሙ በተሰጣቸው ኀላፊነትም ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
መቀመጫን ደቡብ ኮሪያ ባደረገው በዚህ ተቋም ኀላፊነት ማግኘታቸው ለክልሉም ኾነ ለሀገሪቱ ትልቅ ዕድል መኾኑንም ጠቁመዋል። ሹመቱንም እንደ ክብር ሳይኾን እንደ አደራ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል።
የተሠጣቸውን ኀላፊነት መሠረት በማድረግ የባሕል እና ኪነ ጥበብ ዘርፉን ከኢትዮጵያ እስከ ኮርያ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ላይ ለማገናኘት ተልዕኮዎችን በመውሰድ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የኪነ ጥበብ ዘርፍ ወደ ቢዝነስ እንዲያድግ የድርሻየን ለመወጣት ዕድል የሚፈጥር ነውም ብለዋል። የኪነ ጥበብ ቱሪዝም እንዲዳብር የተለያዩ የኤግዚቢሽን መድረኮችን እና ፌስቲቫሎችን ለማጠናከር ጥረት እንደሚያደርጉም አመላክተዋል።
ለረጅም ዘመን የዘለቀውን የኢትዮጵያ እና የኮርያን ግንኙነት በባሕል እና ኪነ ጥበብ የበለጠ ለማስተሳሰር ጥረት እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
ከዚህ በፊት የነበሩትን ልምዶች በመጠቀም በኢትዮጵያ ያለው ብዝኀ ባሕል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጎልቶ እንዲወጣ የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡም ተናግረዋል።
አቶ ገብረ ማርያም ከዚህ በፊት በባሕል እና ኪነ ጥበብ ዘርፉ ከባለሙያነት እስከ ከፍተኛ መሪነት አገልግለዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
