
አዲስ አበባ : መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ስርጭት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት፣ ለሰላም፣ ለእኩልነት እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ሥጋት መኾኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል አዲስ ደንብ እና መመሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ባለፈው አንድ ዓመት የሚዲያ ሞኒተሪንግ እና ጥናት ማድረጉን ተናግረዋል። በዋናነት አምስት የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም፣ ኤክስ እና ዩቲዩብ ላይ ትኩረት በማድረግ ክትትል አድርጓል ነው ያሉት።
በናሙና ከታዩ 32 ሺህ ይዘቶች ውስጥ ከ8 ሺህ በላይ የሚኾኑት የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ይዘት ያላቸው ኾነው መገኘታቸውን አስረድተዋል።
ከአለፉት ዓመታት አንጻር የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ ይዘቶች ስርጭት በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ታግዞ በመሰራጨቱ ምክንያት መጠኑ በ4 በመቶ እንዲጨምር አድርጎታል ብለዋል።
በሰባት ከተሞች በተሠበሠበ የሕዝብ አስተያየት መጠይቅ መሠረት ዜጎች መረጃን በስፋት የሚያገኙት ከእነዚሁ አምስት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች መኾኑ ነው ያብራሩት።
ባለሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1185/2012 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃዎች ሪፖርት በቀረበላቸው በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲያነሱ ክትትል መደረጉንም ገልጸዋል።
ችግሩን ለመከላከል በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የታገዘ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት እና ዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓት እየተገነባ መኾኑንም ተናግረዋል።
በነፃ ስልክ መስመር 9192 አማካኝነት ኅብረተሰቡ መረጃዎችን እንዲጠቁም በማድረግ የመለየት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የጥላቻ ንግግሮች እና ሐሰተኛ መረጃዎች በመጭው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሥጋት እንዳይደቅኑ የፕላትፎርም አገልግሎት ሰጭዎች ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ባለሥልጣኑ በሐሰተኛ መረጃ አሰራጮች ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
