“ጥፋት እና ጠላት ናፋቂ መኾን አይገባም”ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

4
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት በሰሜን ወሎ ዞን ከተውጣጡ ተጽዕኖ ፈጣሪ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ውስጣችንን በመፈተሽ፤ ባሕላዊ እሴቶቻችንን በመጠበቅ እና አጉልቶ በማውጣት ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል ብለዋል።
የሰላም እጦት በሀዘን እና በደስታ እንዳንገናኝ ያደረገን በመኾኑ ሰላምን ለማጽናት የበኩላችንን እንወጣለን ነው ያሉት። አለመተባበር፤ አለመደማመጥ እና መለያየት ዋጋ እያስከፈለን ነው ያሉት ነዋሪዎቹ አንድነትን ማስቀደም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እንዲሠራም ጠይቀዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ሻምበል ፈረደ የታጣቂ ኀይሎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመኾን በአማራ ክልል ላይ ጉዳት እያደረሱ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በሰላማዊ መንገድ እንጅ በግጭት አይደለም ያሉት አዛዡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
የታጣቂ ኀይሎች ለአማራ ሕዝብ የአፈር ማዳበሪያ እና የነዳጅ አቅርቦት እንዳይዳረስ፤ ሕዝቡ ለከፋ የኑሮ ውድነት እና ችግር እንዲጋለጥ እያደረጉ በመኾኑ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ ልትሠሩ ይገባል ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር ማኅበረሰቡ ለአካባቢው ሰላም የመፍትሔ ምንጭ ሊኾን እንደሚገባ ተናግረዋል። ውስጥን በማየት አመለካከትን በማረም ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ ግጭቱ ባሕላዊ እሴትን፣ አብሮነትን፣ መከባበርን እና የሕዝብ ግንኙነትን እያጠፋ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን ከማድረስ ባሻገር የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታ እንዳሄዱ በማድረግ በትውልዱ ላይ ኪሳራ እያደረሰ እንደሚገኝ አንስተዋል። የታጣቂ ቡድኑ ሥልጣንን በኅይል ለመቆጣጠር ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ጫካ የወጣ ኀይል እንጅ የአማራ ሕዝብን ጥያቄ አንግቦ የወጣ አይደለም ነው ያሉት።
ከጥላቻ ንግግር እና ግጭት ቀስቃሽ ከኾኑ ነገሮች በመራቅ ሰላምን ለማጽናት ልትሠሩ ይገባል ብለዋል። ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶችን መጠቀምም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የጠላት ተላላኪዎች የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት ለመናድ እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች ለዘላቂ ሰላም መጽናት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም አሳስበዋል።
በመደራጀት፤ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የታጣቂ ኀይሎችን በማውገዝ እና ከመንግሥት ጎን በመኾን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
ታጣቂዎች ሕዝባዊ እና ሕጋዊ መንግሥት በምርጫ ሂደት እንዳይመሠረት እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ጥፋት እና ጠላት ናፋቂ መኾን እንደማይገባ አሳስበዋል። ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም በቁርጠኝነት ሊያጸና እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ግጭቱ የሚያስከትለውን ጉዳት ማስቆም ይገባል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ የሰላም መደላድልን መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሰላም በጠመንጃ አይረጋገጥም፤ ሰላም የሚረጋገጠው በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ሀቀኛ እና ዕውነተኛ ውይይት ሲካሄድ ነው ብለዋል።
ሁሉም ለሰላም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት ተኪ ምርት እንዲያድግ አስችሏል።
Next articleበሐሰተኛ መረጃ አሰራጮች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን አስታወቀ።