በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት ተኪ ምርት እንዲያድግ አስችሏል።

3
አዲስ አበባ: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ አማካኝነት በተኪ ምርት ዘርፍ ተጨባጭ መሻሻሎች መታየታቸው ተገልጿል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተሠራው የተቀናጀ ሥራ የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ድርሻ 45 ነጥብ 82 በመቶ ደርሷል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት በውጭ ምንዛሬ ቁጠባ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። በ2010 በጀት ዓመት የውጭ ምንዛሬ ማዳን የተቻለው 640 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር። በ2018 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ ግን ይህ ቁጥር ወደ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።
በተኪ ምርት ዘርፍ የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች የመንግሥት ድጋፍ እና የፖሊሲ ለውጡ ለውጤታማነታቸው መሠረት መኾኑን ገልጸዋል።
የዮሴፍ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤት አቶ ዮሴፍ ታደሰ በምግብ እና ምግብ ነክ ዘርፍ መሠማራታቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል። ላለፉት 25 ዓመታት በዘርፉ ቢቆዩም ከለውጡ በፊት በነበረው ደካማ ቅንጅታዊ አሠራር ውጤታማ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል።
አሁን ግን በመንግሥት ልዩ ትኩረት ምርታማነታቸው መጨመሩን እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት መቻላቸውን ተናግረዋል።
የኬርመንት ጋርመንት ፋብሪካ ኀላፊ ኩመራ ኃይለኢየሱስ በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ መሠማራታቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል። ቀደም ሲል ለሀገር ውስጥ ምርት የነበረው ዝቅተኛ የሸማቾች ፍላጎት ተቀይሮ አሁን ላይ የምርቶቻቸው ተፈላጊነት እና ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሻሻል የታየበት በዋናነት በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በተፈጠረው የተቀናጀ አሠራር መኾኑም ተመላክቷል።
ይህም አምራቾች ለገበያ የሚያቀርቡት የምርት መጠን እንዲያድግ እና ሀገሪቱ ለውጭ ምርቶች የምታወጣውን ከፍተኛ ወጭ እንድትቀንስ አስችሏታል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየበልግ ወቅትን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች፦
Next article“ጥፋት እና ጠላት ናፋቂ መኾን አይገባም”ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)