የበልግ ወቅትን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች፦

12
ባሕር ዳር: መጋቢት18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የበልግ ወቅትን ተከትሎ ሊከሠቱ የሚችሉ 10 የጤና ሥጋቶች መለየታቸውን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳውቋል።
ከእነዚህም መካከል ​ዋነኞቹ ወባ እና ኮሌራ ሲኾኑ ​ኩፍኝ፣ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ፣ እከክ እና በጎረቤት ሀገራት የታየው የማርበርግ ቫይረስ ይገኙበታል።
ኢንስቲትዩቱ ሥጋቶችን የለየው ያለፉ ዓመታትን የበሽታዎችን ሥርጭት መረጃዎች መሠረት በማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ባስቀመጠው መለኪያን መሠረት መኾኑን አቶ አበበ ገልጸዋል።
​የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመኸር ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ሥጋቶችን እና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ መኾኑን አስታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት አሥተባባሪ አበበ ሲሳይ ኢንስቲትዩቱ በ36 በሽታዎች ላይ ቀጣይነት ያለው ክትትል እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 22ቱ ወዲያውኑ ሪፖርት የሚደረጉ ሲኾኑ 14ቱ ደግሞ በየሳምንቱ ሪፖርት እየተደረገባቸው ክትትል የሚደረግባቸው ናቸው።
እሥተባባሪው እንዳሉት የበሽታዎችን ሥርጭት በቅርበት ለመከታተልም ጠንካራ የቅኝት (Surveillance) ሥርዓት ተዘርግቷል። ማንኛውም የጤና አደጋ ቢከሰት ፈጣን እርምጃ መውሰድ የሚያስችል “የአደጋ ጊዜ ምላሽ ቅድመ ዝግጅት ዕቅድ” ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ችግሮች ሲከሰቱም ከአንድ ማዕከል ኾኖ ለመምራት የአደጋ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል የሚቋቋም ይኾናል ብለዋል ።
​ተግባሩን ​ከውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ፣ ከአካባቢ፣ ደን እና ዱር እንስሳት ጥበቃ፣ የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮዎች፣ ከአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን እና ​እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ካሉ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
​በሽታን የመከላከል ሥራ ስኬታማ የሚኾነው በኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ነው ያሉት አሥተባባሪው ማንኛውም አዲስ የጤና ችግር ወይም ያልተለመዱ ምልክቶች ሲታዩ ኅብረተሰቡ ለጤና ተቋማት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ ማካሄድ ጀመረ።
Next articleበአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት ተኪ ምርት እንዲያድግ አስችሏል።