
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያዘጋጀው የክርክር መድረክ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሠብሣቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ቦርዱ የክርክር መድረኩን ያዘገጀው የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ፣ ገለልተኛ እና ፍትሐዊ በኾነ መንገድ ፖሊሲዎቻቸውን እና ፕሮግራሞቻቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክን ለመፍጠር መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር መራጩ ሕዝብም በዛው ልክ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን የመስማት ዕድል ኖሮት እንዲወሥን ለማስቻል በማሰብ ነው ብለዋል።
የክርክር መድረኩ እየተካሄደ ያለውን የመራጮች ምዝገባ የበለጠ እንዲነቃቃ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
መራጮችም የመራጮች የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ከመጠናቀቁ በፊት ተመዝግበው ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር በመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች፣ በፖለቲካ ምሁራን እና በጥናት ባለሞያዎች ተሣትፎ ለወራት ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግበት እንደነበር አንስተዋል። ጥያቄዎቹም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፕሮግራም እና ማኒፌስቶ መሠረት አድርገው የተዘጋጁ ናቸው ተብሏል።
ለክርክሩ የተመረጡ ርዕስ ጉዳዮች አስቀድሞ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተልከው ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ተደርጓል። በአከራካሪነት እና በጠያቂነት የሚሣተፉ ባለሞያዎችም ዝርዝር ተልኮ የማሳወቅ ሥራ ተሠርቷል ነው የተባለው።
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በክርክሩም ወቅት የተነገሩ ሃሳቦችን እውነትነት የማረጋገጥ ሥራ የሚሠሩ ባለሞያዎች እንዲሣተፉ ተደርጓል ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
