
ፍኖተሰላም: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከቡሬ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች የጸጥታ ችግሩ ሁለንተናዊ ጉዳት እያደረሰ መኾኑን ተናግረዋል። መንግሥት በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወኑ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ከጸጥታ ችግሩ ባሻገር የኑሮ ውድነቱ የከፋ ጉዳት እያደረሰ መኾኑን ተናግረዋል። የመብራት ኃይል ችግር እንዲፈታም ጠይቀዋል። መንግሥት ለሰላም ሁኔታው ቅድሚያ እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
ምርጫ ለአንድ ሀገር ወሳኝ እና ሕጋዊ ውክል ያለው አሥተዳደር እንዲኖር ሚናው ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ ኅብረተሰቡ እና መንግሥት በመቀናጀት ባከናወኑት ተግባር ከሌሎች አካባቢዎች የተሻለ ሰላም መስፈኑን አንስተዋል።
ከተለያዩ የሀገር ጠላቶች ጋር ተሰልፈው ክልሉን ወደ ከፋ ውድመት እንዲገባ እያደረጉ ያሉ ኀይሎችን ኅብረተሰቡ በቃ ሊል ይገባል ብለዋል።
የዞኑን የመብራት ኀይል ችግር ለመፍታት በቡሬ ከተማ እየተገነባ ያለውን የኀይል ማስፋፊያ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጫናዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተገቢ ያልኾነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል። የክልሉ መንግሥት ለሰላም መስፈን አሁንም ሰላማዊ አማራጮች ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራም ጠቁመዋል። ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም በሰላም እንዲከናወን እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) መንግሥት እያከናወነ ያለውን የሰላም ማረጋጋት ሥራው ዘላቂ እንዲኾን ኅብረተሰቡ አሁንም የሰላም ባለቤት መኾን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ኅብረተሰቡ ዕውነትን አጥብቆ በመያዝ እና ለሀገር ጥቅም ዘብ በመቆም መሥራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ላይ ያለውን የውኃ ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ተናግረዋል። የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በሚፈለገው ልክ እንዲከናወኑ ሰላሙ ላይ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
