በትግራይ ክልል ሊካሄድ የነበረውን የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ በአዲስ አበባ ለማድረግ መወሰኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

7
አዲስ አበባ: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ሊካሄድ የነበረውን የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሠባሠብ ተግባር በአዲስ አበባ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል።
የምክክር ሂደቱን በክልሉ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አስቻይ ሁኔታዎች አለመፈጠራቸውን በምክንያትነት አንስቷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ወቅታዊ የኮሚሽኑን ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የትግራይ ክልል ተሳትፎ ከሌለበት ውጤታማ እንደማይኾን ገልጸዋል። በክልሉ እና በመዲናዋ ያሉ የትግራይ ተወላጆች በአዲስ አበባ ሊካሄድ በታቀደው መድረክ ላይ ተሳታፊ እንዲኾኑም ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚሽኑ የአለመግባባት መንስኤ የኾኑ ችግሮችን ለመለየት እና አካታች ምክክርን ለማድረግ ሢሠራ መቆየቱን ዋና ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።
በዚህም በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተሠርተዋል ነው ያሉት። ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ በሂደቱ የትግራይ ክልልን ለማካተት 22 መድረኮችን በማመቻቸት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አለመሳካቱን ነው የገለጹት።
ይህ አስቻይ ሁኔታ በሌለበት የክልሉ ተወላጆች በምክክሩ የመሳተፍ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ለማድረግ በማሰብም ከመጋቢት 23 እስከ 25/2018 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ የሚደረግ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ለዋናው የምክክር ጉባኤ የተሳታፊ ልየታ ለማከናወን የሚያስችል መድረክ ማዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።
ለዚህ ያመች ዘንድ በክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ መንግሥታዊ አካላት፣ ልዩ ልዩ ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተወካይ ጥሪ ያደርጋል ብለዋል። ኮሚሽኑ በመዲናዋ የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጅ የኾኑ ተሳታፊዎችን በበይነመረብ ለመመዝገብ ማቀዱንም ገልጿል።
በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንዲኾኑሞ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleማንነትን መሠረት ያደረገ የሳይበር ጥቃት ሥጋት ጨምሯል።
Next articleወላጆች እና አሳዳጊዎች ሕጻናትን የፖሊዮ ክትባት ማስከተብ አለባቸው።