
ባሕር ዳር: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት በሰሜን ወሎ ዞን ከተውጣጡ ተጽዕኖ ፈጣሪ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያካሄዱ ነው።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የዞኑ ሕዝብ በሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ደርሶበታል ነው ያሉት።
መንግሥት የሰላም አማራጮችን በማቅረቡ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ተናግረዋል።
የጥፋት ኀይሎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር ችግር እየፈጠሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የጥፋት ኀይሎቹ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዳይካሄድ ለማድረግ እና የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዳያገኝ እንቅፋት ለመፍጠር እየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል።
በዞኑ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በጋራ ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ግጭት እና ጦርነት እስካለ ድረስ የሰላም መደላድል መፍጠር አስቸጋሪ ነው ብለዋል።
የሰላም መደላድል ካልተፈጠረ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ዜጎች የዴሞክራሲ ተጠቃሚነታቸው የማይረጋገጥበት ይኾናል ነው ያሉት።
የፖለቲካ ሥርዓቱ የሰከነ ኾኖ ለመግባባት እና ለመተማመን የሚያስችል መሠረት እንዲጣል ሰላምን ማጽናት የመጀመሪያ ሥራ ሊኾን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተደጋጋሚ ስለ ሰላም መምከር ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ዋስትና ነውም ብለዋል።
ውይይቱ የሕዝብን ሃቀኛ እና ዕውነተኛ ሚና በመለየት ለመተግበር የሚደረግ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከውይይቱ ግብዓትን በመውሰድ ማኅበረሰቡ ለሰላም የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
