ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ማላቦ ኢኳቶሪያል ጊኒ ገቡ።

2

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በ11ኛው የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ ማላቦ ኢኳቶሪያል ጊኒ ገብተዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ማላቦ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢኳቶሪያል ጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ኡሳ ኡዙዌን ጨምሮ የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት ከ5 አስርት ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ1975 በቶጎ በተካሄደው ሎሜ ኮንቬንሽን ነበር የተጠነሰሰው፡፡

በሰኔ ወር በዚያው ዓመት ደግሞ ከአፍሪካ፣ካርቢያን እና ፓሲፊክ የተወጣጡ 46 ሀገራት በፈረሙት የጆርጅታውን ስምምነት መሰረት ድርጅቱ ተመስርቷል።

በተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች ያለፈው ድርጅቱ አሁን ላይ 79 ሀገራትን በአባልነት ማካተት የቻለ ሲኾን የተፅዕኖ ደረጃውም በዚያው ልክ እያደገ ነው የመጣው።

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከንግድ እና ኢኮኖሚ ትብብር በተጨማሪ የልማት ፣ዴፕሎማሲ፣ ፖለቲካዊ እና ዓለም አቀፍ የፍትሕ ጉዳዮች የሚንሸራሸሩበት መድረክ እየኾነ መጥቷል።

11ኛው የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመጋቢት 18 እስከ 20 /2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

ኢዜአ እንደዘገበው ከሦስቱም ክልሎች የሚገኙ የሀገራት መሪዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኀብረት እና የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበልማት የታዩ ስኬቶችን ወደ ሌሎች የአሥተዳደር ዘርፎች በማሸጋገር ውጤታማነትን ማረጋገጥ ይገባል።