
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያሉ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ጸጋዎችን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
የተጀመሩ ውጤታማ የአትክልት እና ፍራፍሬ ሥራዎች ለሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ጭምር ትልቅ አቅም በመኾናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት።
በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት የታዩ ስኬቶችን ወደ ሌሎች የአሥተዳደር ዘርፎች በማሸጋገር ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በዞኑ በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት ለልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም አመላክተዋል።
የሕግ የበላይነት በማስከበር የአካባቢውን ሰላም እና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በውስጣዊ የሰላም እና የጸጥታ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ከአጎራባች ዞኖች ጋር የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ለኢንቨስትመንት ዕድገት ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በበጀት ዓመቱ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ከኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው እስካሁን የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል እና በሚታዩ ክፍተቶች ላይ ርብርብ በማድረግ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
