ምሁራን በችግር ጊዜ መፍትሔ አመላካች ጥናት እና ምርምሮችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

4

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳዳር በወቅታዊ የሰላም እና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሠራተኞች ጋር ውይይት አድርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊ ምርታቸው ጣሒር (ዶ.ር) ዕውቀት እና ጥበብን መሠረት በማድረግ ትውልድ ለመቅረጽ እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የድረሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል። በችግር ጊዜ ደግሞ መፍትሔ ተኮር ሥራዎችን መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ዳዊት ተሰማ (ዶ.ር) ሰላም ከራስ ይጀምራል፤ ለሕሊና ሕግም መገዛት ይገባል ብለዋል። ምሁራን በማስተማር፣ በምርምር እና በተለያዩ አማራጮች ስለሰላም ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ዓለም ያለበትን ሁኔታ በመረዳት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መፍትሔ በማመላከት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርት የወለደውን ዳፋ ለመቋቋም እንደ ሀገር ተመራማሪዎች ሀሳብ በማመንጨት ወደ ተግባር መለወጥ ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ምሁራን የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስኑ ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዕውቀት ላይ ተመስርተው ክልሉን ከግጭት አዙሪት በማውጣት ዘላቂ ሰላም እንዲፀና ሊሠሩ እንደሚገባ አመላክተዋል። የውስጥ ግጭት መፍትሔ እንዲያገኝ እና ልማት እንዲፋጠን ምሁራን በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በመማር ማስተማር የሰላም አምባሳደር ዜጎችን ማፍራት፣ የችግሮች መፍትሔ አመላካች ጥናት እና ምርምሮችን መሥራት ከምሁራን እንደሚጠበቅ ነው ያስረዱት። ምሁራን ዛሬን መሥራት፣ ነገን መተንበይ እና ሀገር በቀል እሴቶችን ለማኅበረሰቡ ማስገንዘብ ይገባቸዋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሀኑ ጎሽም ምሁራን ለዘላቂ ሰላም ችግሮችን ከመለየት ባለፈ ግብረ ገብነት የተላበሰ ትውልድ ማነጽ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ፍትሐዊ እና ሰላማዊ ኾኖ እንዲከናወን በማድረግ በኩልም ሚናቸው ከፍ ያለ መኾኑን ነው ያነሱት።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው መንግሥት ሰላምን ለማጽናት ተደጋጋሚ የሰላም አማራጭ ጥረቶች ማድረጉን እንስተዋል። አሁንም ለውይይት ዝግጁ ነው ብለዋል። ምሁራን ታሪክ እና ትርክትን በውል ተረድተው ማስታረቅ ይገባቸዋል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከፈተና በመውጣት በተረጋጋ ሰላም ለመቆም ሁሉም በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግጭት እና ጦርነትን የማይመግብ አመለካከት መያዝ ይገባል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleበልማት የታዩ ስኬቶችን ወደ ሌሎች የአሥተዳደር ዘርፎች በማሸጋገር ውጤታማነትን ማረጋገጥ ይገባል።