“ግጭት እና ጦርነትን የማይመግብ አመለካከት መያዝ ይገባል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

3

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከወልድያ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር በሰላም እና በልማት ዙሪያ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም እጦቱ በሴቶች ሕጻናት እና አረጋውያን ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።

ግጭቱ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን፣ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ፣ ነብሰ ጡር እናቶች ወደ ጤና ተቋማት እንዳይሄዱ ማድረጉን እና በሌሎችም ዘርፎች ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። ከልብ ለሰላም መትጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በከተማዋ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ሕዝቡን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል። የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ እንዲኾን፣ ብልሹ አሠራር እንዲቀር፣ መንግሥት የኑሮ ውድነትን እንዲቆጣጠር፣ የሕዝብ ተሽከርካሪ አገልግሎትን እንዲፈትሽም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የዕውነት እና የሉዓላዊነት ጉዳይ በመኾኑ የበኩላችንን ኀላፊነት እንወጣለን ብለዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ማኅበረሰቡ ያነሳቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል። የከተማዋን ልማት ለማፋጠን በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ የክልሉ መንግሥት የወልድያን ከተማ ልማት ለማፋጠን እና ማኅበረሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራቱን ተናግረዋል።

ልማትን የሚያጠፋ፣ ኢንቨስትመንትን የሚያርቅ፣ ጎብኝዎችን የሚያስቀር የግጭት አመለካከትን ከውስጥ በማራቅ ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት የሰላም ጥሪ በማቅረቡ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን አንስተዋል። የመንግሥት የሰላም በር አሁንም ክፍት መኾኑን ገልጸዋል። ለሕግ እና ሥርዓት በመገዛት፣ ጥላቻን ከሚዘሩ ንግግሮች በመራቅ እና በምርጫ ሂደት ተሳታፊ በመኾን ሰላማችሁን ልታጸኑ ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) መንግሥት ከታጣቂዎች ጋር የሰላም ስምምነት በመፈጸም፣ የተሃድሶ ሥልጠና በመስጠት እና መልሶ በማደራጀት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ብለዋል።

ሰርጎ ገብነትን እና የከተማ ሽፍቶችን ከመንግሥት ጎን በመኾን በመቆጣጠር ሰላምን ለማጽናት ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት። የታሪካዊ ጠላቶች ሴራን ለማክሸፍ የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፤ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ተሳታፊ ልትኾኑ ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የወልድያ ከተማ በልማት እየታደሰች ነው ብለዋል። በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች ነገን ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ ችግር እየተፈጠረ በመኾኑ በቀጣይ ታች ድረስ በመውረድ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሠራ አብራርተዋል።

ሁከት፣ ግጭት፣ ጦርነትን የማይመግብ አመለካከት እና ድርጊት በመያዝ የሰላም ባሕል ባለቤት ልትኾኑ ይገባል ነው ያሉት። የውስጥ ሰላምን በማጽናት እና ራስን በማድመጥ የሰላምን ባሕል ልትገነቡ ይገባል ብለዋል።

በከተማው የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ተደራጅቶ አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ የልማት ተሳታፊ እንዲኾን እና አስቻይ የምርጫ ኹኔታን እንዲፈጥር አሳስበዋል።

ነዋሪዎቹ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዲመዘገቡ፣ የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ፣ ሕዝብ እና ሀገርን ይጠቅማል የሚሉትን ፓርቲ እንዲመርጡም አስገንዝበዋል። ሀቀኛ እና ዕውነተኛ ምክክር በማድረግ ለሰላም መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፋይዳ ለአገልግሎት ሰጭም ኾነ ለአገልግሎት ፈላጊ መሠረታዊ ነው።
Next articleምሁራን በችግር ጊዜ መፍትሔ አመላካች ጥናት እና ምርምሮችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል።