
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም(አሚኮ) እንደ ሀገር ዜጎች የፋይዳ (ዲጂታል) መታወቂያ እንዲያወጡ ግብ ተይዞ በንቅናቄ እየተከናወነ ይገኛል።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደርም ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ማኅበረሰቡ በንቅናቄ እንዲያወጣ እየተደረገ ይገኛል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት መኩሪያ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ32 ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥም 31 ሺህ 818 የሚኾኑት ወይንም 98 በመቶ ሠራተኞቹ ፋይዳ መታወቂያ አውጥተዋል ነው ያሉት።
በቀጣይ ጊዜያት ቀሪ የመንግሥት ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ ፋይዳ እንዲያወጡ ንቅናቄው ይቀጥላል ብለዋል ኀላፊዋ።
ፋይዳ ለአገልግሎት ሰጭም ኾነ ለአገልግሎት ፈላጊ መሠረታዊ በመኾኑ ሁሉም ዜጎች መያዝ አለባቸው ብለዋል። አርሶ አደሮችም ጭምር የመታወቂያው ባለቤት እንዲኾኑ እና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ በትኩረት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
በአሥተዳደሩ በማኅበረሰብ ደረጃ 444 ሺህ 193 ሰዎች መታወቂያውን እንዲይዙ ዕቅድ የተያዘ ሲኾን እስካሁንም 247 ሺህ 489 ሰዎች ፋይዳ መታወቂያ አውጥተዋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ሰለሞን ስንታየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
