ምርጫ ሀገራትን ከቀውስ ወደ ሰላም እንዴት አሸጋገራቸው?

5
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በታሪክ ውስጥ ምርጫ ግጭቶችን ከጦር ሜዳ ወደ ድምፅ መስጫ ሳጥን በማሸጋገር ሀገራትን ከከፋ ውድቀት ለመታደግ የሚያስችል ተቋማዊ መሣሪያ ነው።
የቀድሞው የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሀንቲንግተን ምርጫን የጦርነት ምትክ በማለት እንደሚገልጹት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተመራማሪዎች፣ ሳይንቲስቶች እና ምሁራን የጥናት ውጤቶቻቸውን በሚያጋሩበት እና እርስ በእርስ በሚገናኙበት ትልቁ የምሁራን ማኅበራዊ ትስስር ድረ-ገጽ ሪሰርች ጌት (ResearchGate.net) ላይ የወጣው ጥናታዊ ጽሑፍ ያስረዳል፡፡
በኅብረተሰብ ውስጥ ለሥልጣን የሚደረገው ትግል በኃይል እና በአውዳሚ ድርጊቶች ፈንታ በተደራጀ፣ ሰላማዊ እና ሕጋዊ በኾነ ውድድር እንዲተካ ስለሚያደርግ ነው የሚለውን በመግለጫነትም ያነሳሉ። ይህ ሂደት ግላዊ ፍላጎቶችን ወደ አንድ የጋራ ውጤት የሚቀይር ውስብስብ ሳይንሳዊ ሂደት በመኾኑ የፖለቲካ አለመግባባቶችን በሥርዓት ለመፍታት የሚያስችል መዋቅራዊ መድረክ ይፈጥራል ይላል።
ከእርስ በርስ ግጭት የወጡ ሀገራት የምርጫን ፋይዳ የሚረዱት እንደ አንድ የፖለቲካዊ መተንፈሻ እና የሰላማዊ ሥልጣን ሽግግር መሣሪያነት ነው። ለዚህም የደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ የ1994 የመጀመሪያው ሁሉን አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዋነኛ ማሳያ መኾኑን መቀመጫውን በስዊድን ያደረገው የሰላም ምርምር ተቋም ሲፕሪ “ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ወደ ብዙኃ ፓርቲ ዴሞክራሲ” በሚል በድረ ገጹ ያጋራው ዘገባ ያሳያል፡፡
ሀገሪቱ ከአፓርታይድ ሥርዓት ወደ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንድትሸጋገር በማድረግ፣ የታጠቁ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በጠመንጃ ሳይኾን በምርጫ ካርድ እንዲፈቱ አስችሏል የሚል ነው።
በንጽጽራዊ ፖለቲካ፣ በምርጫ እና በድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቶች፣ በተቋማት፣ በብሔር እና በፖለቲካ ግንኙነት ላይ ሰፊ ጥናቶችን በማድረግ የሚታወቁት ፕሮፌሰር አረንድ ሊጅፋርት “የስምምነት ዴሞክራሲ” በሚለው ዕይታቸው ምርጫ ሰላም ሊያመጣ የሚችለው ሁሉም ወገኖች ራሳቸውን የሚያገኙበት ተመጣጣኝ ውክልና ሲኖር መኾኑን አመላክተዋል፡፡
ደቡብ አፍሪካም አሸናፊው አካል ሁሉንም ያካተተ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲመሠረት ማድረጓ “ምርጫ ወደ ሰላም የመሸጋገሪያ አንዱ መንገድ መኾኑን” አረጋግጣለች፡፡
በተመሳሳይ በኤልሳልቫዶር የታጠቁ አማጽያን ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ተቀይረው በምርጫ እንዲሳተፉ መደረጋቸው በሀገሪቱ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያበቃ ምክንያት መኾኑን በዋናነት በግጭት አፈታት፣ በሰላም ግንባታ እና በዓለም አቀፍ ደኅንነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው እና መንግሥታዊ ያልኾነው የበርግሆፍ ፋውንዴሽን ጥናታዊ ጽሑፍ ያሳያል፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫ በራሱ ብቻውን ለሰላም ዋስትና ሊኾን እንደማይችል የናይጄሪያ ካዱና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጆይ አማራቺ ኦፎርዲ እና ፖል ቲሚሌይን አሌዮሚ የተሠራው ጥናታዊ ጽሑፍ ያረጋግጣል፡፡ ምርጫ ውጤታማ የሚኾነው እንደ ተራ የጊዜ ሰሌዳ ሳይታይ የሂደቱ ጥራት እና አካታችነት ሲረጋገጥ ብቻ እንደኾነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ኾነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ጃክ ስናይደርን ምርጫ ሰላም ማምጣት የሚችለው የምርጫ አሥፈጻሚዎች ገለልተኝነት ሲረጋገጥ፣ በፓርቲዎች መካከል በጨዋታው ሕግ ላይ ቅድመ ስምምነት ሲኖር እና የጸጥታ ዋስትና ሲሰፍን ብቻ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ ምርጫ የዴሞክራሲ ማብቂያ ሳይኾን ጅምር በመኾኑ ሰላም የሚረጋገጠው የተሰጠው ድምጽ ሲከበር እና የአናሳ ወገኖች መብት ጥበቃ ሲደረግለት እንደኾነ በምሁራኑ ጥናት እና በተግባራዊ የሀገራት ተሞክሮዎች ተመላክቷል።
ኢትዮጵያም በመጭው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም የምታካሂደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ከምርጫ ባለፈ ግጭቶች በሰላማዊ እና የፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ የሚፈቱበት እንዲኾን እያንዳንዱ ዜጋ ድምጼ ዋጋ አለው ብሎ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል፡፡
ለዚህም የምርጫ ቦርድ፣ የፍትሕ አካላት እና የጸጥታ ተቋማት ገለልተኛ ኾነው እንዲሠሩ በማድረግ ዜጎች በሂደቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የምርጫ ካርድ እየወሰድን፤ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚበጀውን ተመራጭም እየለየን ነው” የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች
Next articleፋይዳ ለአገልግሎት ሰጭም ኾነ ለአገልግሎት ፈላጊ መሠረታዊ ነው።