
ሰቆጣ: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመጭው ግንቦት ወር የሚካሄደውን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች የመራጭነት ካርዳቸውን ቀድመው በመውሰድ ለምርጫው ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል። ዜጎች በአካል በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት እና በዲጂታል አማራጭ በ”ምርጫዬ” መተግበሪያ አማካኝነት ምዝገባቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ።
የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው ወጣት መለሰ ቦጋለ እና ወይዘሮ እልፍነሽ አዲሱ የመራጭነት ካርዳቸውን ቀድመው ማውጣታቸው ለሀገር የሚጠቅመውን የፖለቲካ ፓርቲ በሰከነ ሁኔታ ለይተው ለመምረጥ ዕድል እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። ሰላማችንን አጽንተን የሚበጀንን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ ሌሎች ነዋሪዎችም የምዝገባው ቀነ ገደብ ሳይጠናቀቅ ካርዳቸውን እንዲያወጡም መክረዋል። የምርጫ ካርድ እየወሰድን፤ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚበጀውን ተመራጭም እየለየን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ማርዬ ባለፈው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ጭምር በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግን ምርጫው እንዲካሄድ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። ዜጎች የሚወክላቸውን እና የሚመራቸውን መንግሥት ለመምረጥ ድምጽ መስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ መያዝ ግዴታ መኾኑን ያመላከቱት ኀላፊው ሰላማዊ ምርጫን ለማካሄድ ሁሉም በጋራ ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የካቲት 28/2018 ዓ.ም የጀመረው የመራጮች ምዝገባ ሂደት እስከ መጋቢት 28/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ መኾኑን ገልጸው መራጮች በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ምዝገባቸውን አጠናቅቀው ለምርጫው ቀን እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
