ከ70 በላይ ሀገራት… 800+ ባለሀብቶች… በአንድ መድረክ!

11
አዲስ አበባ: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከ71 ሀገራት በላይ የተውጣጡ ከ800 በላይ ባለሃብቶች፣ የቢዝነስ መሪዎች እና አማካሪዎች የተሳተፉበት አራተኛው ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2026 ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፎረም “ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ናት” በሚል መሪ መልዕክት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በርካታ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን አድርጋለች።
ይህም የፋይናንስ እና የቴሌኮም ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ እንዲኾኑ አድርጓል ብለዋል። የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በውጭ ምንዛሪ ላይ ሪፎርም ማድረግን ጨምሮ ዓለም አቀፉን የኢንቨስትመንት ፍላጎት የሚያሟሉ የመሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል ነው ያሉት።
ለዚህም የኢንቨስትመንት ዞኖች እና የእንዱስትሪ ፓርኮች ተጠቃሽ መኾናቸውን ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በቴሌኮም እና በአምራች ዘርፉ ላይም በርካታ የታክስ ማበረታቻዎች እንደተደረጉ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹ ከሁሉም የዓለም ሀገራት ጋር የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲኖር ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የአፍሪካን ኢኮኖሚ እንደገና ለመቅረጽ ልዩ ዕድል ስለመስጠቱም ጠቁመዋል። ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ካፒታል ብቻ ሳይኾን ምርቶችን በነጻነት የማጓጓዝ እና ባለሃብቶችን የመሳብ አንድምታም ያለው ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዘለቀ ተመስገን በፎረሙ ከ70 በላይ ከሚኾኑ የዓለም ሀገራት የመጡ የቢዝነስ አጋሮች እንደተሳተፉ ገልጸዋል። የፎረሙ ዋና ዓላማ የኢንቨስትመንት አቅምን ማሳየት መኾኑንም ተናግረዋል።
ሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ፎረም ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ዕድሎች እና አማራጮች፣ ፖሊሲዎች እና አሁን ላይ እየተተገበረ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማማሻሻያ ያመጣውን ለውጥ ለማስገንዘብ የሚያስችሉ ውይይቶች እና የተለያዩ የጋራ እና የሁለትዮሽ የቢዝነስ ውይይቶች እንደሚደረጉበትም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የኢንቨስትመንት ፍላጎት የሚያሟሉ መሠረተ ልማቶችን ገንብታለች” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleሹዋሊድን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያሳይ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተጠናቅቋል።