“እኛ የምንፈልገው ድጋፍን ሳይኾን አጋርነትን ነው፤ ርዳታን ሳይኾን ኢንቨስትመንትን ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

4
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አራተኛውን ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2026 ( Invest in Ethiopia 2026) የቢዝነስ ፎረምን አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ዝግጁ የኾነች፣ የዕምቅ ዐቅሞችና የዕድሎች መሶብ ናት ብለዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ አራተኛውን ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2026 ( “Invest in Ethiopia 2026”) የቢዝነስ ፎረምን ማስጀመራቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ብቻ አይደለችም፤ ዛሬ በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ ያለች፣ ግዙፍና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እየገነባች የምትገኝ ሰፊና አዋጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት። የኢንቨስትመንት መሶባችን በትጉኅና ወጣት ሕዝብ ዐቅም፣ ባልተነካ የተፈጥሮ ጸጋ እና በስትራቴጂያዊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የታደለ ነው።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርማችንና በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያችን ለዘመናዊና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ የማይመቹ አሠራሮችን በቆራጥነት በመቀየር እንደ ፋይናንስና ቴሌኮም ያሉ ቁልፍ ዘርፎችን ለዓለም አቀፍ ኢንመስትመንት ክፍት አድርገናል።
የመሠረተ ልማት አውታሮችን ማስፋፋታችንና የሕዳሴው ግድብን አጠናቀን አስተማማኝ የኃይል ምንጭ መፍጠራችን ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ምኅዳርና ቁርጠኝነት ለዓለም የሚያረጋግጡ ታላላቅ ማሳያዎች ናቸው።
እኛ የምንፈልገው ድጋፍን ሳይሆን አጋርነትን ነው፤ ርዳታን ሳይሆን ኢንቨስትመንትን ነው! ለባለ ሀብቶች ምቹ፣ ግልጽና ተራማጅ የሆነ የሕግ ማሕቀፍ አዘጋጅተናል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው በግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ፣ በፈጠራና በርትዕ በሚመራ የኢኮኖሚ ምኅዳር መሆኑን በጽኑ እናምናለን።
ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ካፒታል፣ ለችሎታ እና ለዕድል በሯን ወለል አድርጋ ከፍታለች። የዛሬው መድረክም ራዕይን ከተግባር፣ ዕቅድና መሻትን ደግሞ ከኢንቨስትመንት ጋር በማገናኘት የጋራ ብልጽግናችንን የምንቀርጽበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
ኢትዮጵያ አሁን በፍጥነት ወደ ከፍታ እየገሠገሠች ባለችበት በዚህ ታሪካዊ የዕድገት ጉዞ፣ ለዓለም አቀፍና ለሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶች ኢትዮጵያ ለእናንተ ዝግጁ የሆነ፣ በዕድሎችና በስኬቶች የተሞላ ታላቅ የኢንቨስትመንት መሶብ አላት፤ ኑ አብረን እንሥራ!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የሰላምን ባሕል የሚሸረሽሩ ትርክቶችን በማረም አብሮነትን ማስቀጠል ያስፈልጋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next article“ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የኢንቨስትመንት ፍላጎት የሚያሟሉ መሠረተ ልማቶችን ገንብታለች” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ