
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ የሕዝብን ችግር የሚፈቱ እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች በሕዝብ ዘንድ ድምጽ የሚሰጥበት ሂደት መኾኑን በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም ተናግረዋል።
ምርጫ የአንዲት ሀገር የዴሞክራሲ ልምምድ ማሳያ እና ሥልጡን የፖለቲካ ሥርዓት መገለጫ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ልምምድ ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል። ይሁን እንጅ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት እና የፖለቲካ ባሕልን እንደ አደጉ ሀገራት ለማጎልበት ዜጎች በምርጫ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው አንስተዋል።
ይህ ሲኾን እንደ ሀገር የሚፈጠሩ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ ንግግር እና በሠለጠነ መንገድ መፍታት የሚያስችል የፖለቲካ አውድ መፍጠር ይቻላል ብለዋል።
ነገ ሕዝብ ቢመርጠኝ ሀገርን እመራለሁ የሚሉ ፓርቲዎች የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚችሉ የፖሊሲ አማራጮችን ይዘው መቅረብ አለባቸው ነው ያሉት።
ዜጎች በምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ገዥው ፓርቲን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች ዜጎችን መቀስቀስ አለባቸው ብለዋል።
መምረጥ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታም የመፍጠር ኀላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን ከአባላቶቻቸው ጋር መወያየት እና ለኅብረተሰቡ ከወዲሁ ግንዛቤ መስጠት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
እንደ ምሁሩ ገለጻ የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ፣ ተአማኒ፣ ግልጽ፣ ገለልተኛ ፣ አሳታፊ እና አካታች እንዲኾን በትኩረት መሥራት አስፈላጊ ነው።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የመራጮች ምዝገባ አካሂደዋል። የምዝገባ ሂደቱም በዲጂታል እና በወረቀት እየተካሄደ መኾኑ ነው የተገለጸው።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
