የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት እንዴት ለዋጋ መናር ምክኒያት ኾነ?

6
ባሕር ዳር: መጋቢት17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሆርሙዝ ወሽመጥ ከዓለም አቀፉ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ውስጥ 20 በመቶ የሚኾነው የሚያልፍበት የዓለም የኢኮኖሚ የደም ሥር ተደርጎ ይወሰዳል።
እንደ አሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አሥተዳደር (EIA) ግምት በ2025 ዓ.ም በቀን በአማካይ 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እና የነዳጅ ውጤቶች በዚህ ወሽመጥ በኩል ተጉዘዋል። ይህም በዓመት እስከ 600 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ግዙፍ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት መኾኑን ያሳያል።
​ይህ መስመር እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኢራቅ፣ ኩዌት፣ ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላሉ የመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ አምራቾች ዋነኛ መተላለፊያ ነው። ከዓለም የፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ ዝውውር ውስጥም 20 በመቶው በዚህ መስመር ይጓጓዛል። ከነዳጅ ባሻገር ቀጣናው እንደ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ማዳበሪያን እና ቴክኖሎጂ ያሉ ምርቶች የሚተላለፍበትም ነው።
ይኹን እንጅ ከየካቲት ጀምሮ በአሜሪካ፣ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሰርጡ ለከፍተኛ መስተጓጎል ዳርጎታል። ይህ ቁልፍ የባሕር መስመር መስተጓጎል በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ እና ምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ ሥጋት ደቅኗል።
​የሰርጡ መዘጋት እና ተያያዥ ሥጋቶች ያስከተሏቸው ዋና ዋና ተጽዕኖዎች የሚከተሉት ናቸው፦
✍️የመርከቦች ጉዞ መስተጓጎል፦ በወር በአማካይ 3 ሺህ የሚጠጉ መርከቦች ይጓዙበት የነበረው መስመር አኹን ላይ የትራፊክ ፍሰቱ በከፍተኛ ኹኔታ ቀንሷል። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ አንስቶ እስከ መጋቢት መጀመሪያ አካባቢ ቢያንስ 21 መርከቦች የጥቃት ኢላማ ኾነዋል።
✍️የኢንሹራንስ ዋጋ መናር፦ የመርከብ ባለቤቶች ለከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት በመጋለጣቸው የኢንሹራንስ ክፍያ በከፍተኛ ኹኔታ እንዲጨምር አድርጓል። ይህም ብዙ ድርጅቶች ጉዟቸውን እንዲያቋርጡ አስገድዷቸዋል።
✍️የዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል። የነዳጅ ዋጋ መናር በኢነርጅ ምርት ላይ ጥገኛ የኾኑ የባሕረ ሰላጤው ሀገራትን ብቻ ሳይኾን መላውን ዓለም ለኑሮ ውድነት እና ለምጣኔ ሃብታዊ አለመረጋጋት ዳርጓል።
ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የጂኦ ፖለቲካዊ ውጥረት እና የኢነርጂ ቀውስ የኢትዮጵያን የነዳጅ ገበያ እና የሸማቹን የዕለት ተዕለት ሕይወትም መፈተኑ አልቀረም።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፈንታው ፈጠነ ግጭቱ በሀገር ውስጥ ገበያ ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል። ​
መንግሥት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በኅብረተሰቡ ላይ የኑሮ ውድነት ጫና እንዳይፈጠር ​የቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ገልጸዋል።
​ምርትና አገልግሎቶች በቀጥታ ለሸማቹ የሚቀርቡበት አሠራር ተግባራዊ መደረጉንም አንስተዋል። ​”ነዳጅ ሊጠፋ ይችላል” የሚለውን ሥጋት ለመቅረፍ የነዳጅ ክምችቶችን አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ነዳጅ መቀመጥ ያለበት በታወቁ የነዳጅ ማደያዎች ብቻ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ከዚህ ውጭ በማንኛውም መጋዘን ወይም ያልተፈቀደ ቦታ ነዳጅም ኾነ ሌላ ምርት ደብቆ የሚያከማች አካል አሥተዳደራዊ እና በወንጀል ተጠያቂ ይኾናል። የተገኘውም ምርትም በመንግሥት እንደሚወረስ አስጠንቅቀዋል።
የቀረበውን ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ወሳኝ ተግባራት ብቻ ማዋል እንደሚገባም አሳስበዋል።
​ኅብረተሰቡ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ከመቀበል ይልቅ መብቱን እንዲያስከብር እና መሰል ሕገ ወጥ አሠራሮችን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ ቀርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleስለዳሌ አጥንት አንጓ ስብራት ምን ያክል ያውቃሉ ?
Next articleየዴሞክራሲ ልምምድን ለማጎልበት የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።