
ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዳሌ አጥንት አንጓ ስብራት በጭን አጥንት የላይኛው ክፍል መገጣጠሚያ ላይ የሚከሰት የጤና እክል ነው። በአብዛኛው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይ ይከሰታል። በድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት በወጣቶች ላይም ሊከሰት ይችላል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የአጥንት እና መገጣጠሚያ ስፔሻሊስት እና የያኔት ጎንደር ስፔሻላይዝድ የሕክምና ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ጌታነህ ወርቅነህ 80 በመቶ የሚኾነው የዳሌ አንጓ ስብራት ከዕድሜ ጋር በተያያዘ የአጥንት መሳሳት ምክንያት የሚከሰት ነው ብለዋል።
እንደ ዶክተር ጌታነህ ማብራሪያ በአደጋም ይሁን በዕድሜ ምክንያት ብሽሽት መገጣጠሚያ አካባቢ ለማንቀሳቀስ መቸገር፣ በእግር መሬት መርገጥ እና መራመድ አለመቻል፣ ስብራቱ ቦታውን የለቀቀ መኾን፣ የእግር ማጠር የመሳሰሉት የሕመሙ ምልክቶቹ ናቸው ነው ያሉት። እነዚህ ምልክቶች ከታዩ ፈጥኖ ወደ ሕክምና በመሄድ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንደሚያስፈልግም መክረዋል።
በ48 ሰዓታት ውስጥ ሕክምና ካልተደረገ የደም መርጋት፣ ኢንፌክሽን፣ የውስጥ ቁስለት ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል። በዚህም የአልጋ ቁራኛ ያደርጋል፤ ሕመሙ እየጸና ሲሄድም ከኩላሊት፣ ከሳንባ እና ከደም መርጋት ጋር በተያያዘ ለኢንፌክሽን ያጋልጣል፤ ለሞትም ይዳርጋል ነው ያሉት።
ለዳሌ አጥንት አንጓ ስብራት የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ሕክምና አማራጮች እንዳሉም አስገንዝበዋል። የራጅ ምርመራ በማድረግ የስብራት መጠኑ ይለያል፤ የሲቲ ስካን ምርመራ ይደረጋል፤ የአልትራሳውንድ፣ የላበራቶሪ እና ተያያዥ ምርመራዎችም እንደሚደረጉ አብራርተዋል።
ምርመራውን መሠረት በማድረግም በቀዶ ጥገና ይታከማል ነው ያሉት። በዚህም የግማሽ ዳሌ ንቅለ ተከላ(የቅያሬ) እና የሙሉ ዳሌ ንቅለ ተከላ ሕክምናዎች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።
የተሰበረውን አጥንት ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረጉ ሕክምናዎች ውጤታማ የሚኾኑት ታካሚዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ወደ ሕክምና ከመጡ ብቻ መኾኑንም አብራርተዋል። የዳሌ አጥንት አንጓ ስብራት በወጌሻ እንደማይድንም ገልጸዋል።
በተለይም በአጥንት መሳሳት ምክንያት ለሚከሰት የአጥንት አንጓ ስብራትን ቀድሞ ለመከላከል ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ያሉት እናቶች ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
ወጣቶች ደግሞ አመጋገባቸውን ማስተካከል፣ አካላዊ እንቅስቃሴን ማዘውተር፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ አልኮል መቀነስ፣ ሐኪም ሳያማክሩ መድኃኒት ባለመውሰድ በአጥንት መሳሳት ከሚመጣ የዳሌ አጥንት ስብራት ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ መክረዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
