አቢሲኒያ ባንክ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።

4

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቢሲኒያ ባንክ “አችላለሁ” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን በተለያዩ ኹነቶች በባሕርዳር ከተማ አክብሯል።

በኹነቱ የተገኙት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ አቢሲያ ባንክ የላቀ ብቃት እና ክህሎት ያላቸውን ነጋዴ ሴቶች እያበረታታ እና አብሮ እየሠራ እንደኾነ ተናግረዋል።

የላቀ ብቃት ያላቸው ሥራ ፈጣሪ ነጋዴ ሴቶች በብድር አቅርቦት ምክንያት ለሥራ ማነቆ የኾነባቸውን ችግር ለመፍታት በአነስተኛ ወለድ ልዩ የብድር አቅርቦት ማመቻቸቱንም አንስተዋል። ከዚህ ባሻገር ነጋዴ ሴቶች ምርቶቻቸውን ለሸማቾች እንዲያስተዋውቁ እና እንዲሸጡ ባዛር በማዘጋጀት እገዛ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህ ተግባርም ባንኩን አመሥግነዋል።

የአቢሲኒያ ባንክ ባሕርዳር ዲስትሪክት የሃብት አሠባሠብ ሥራ አሥኪያጅ ታየ አካለወርቅ ባንኩ የሴቶችን ቀን በማስመልከት ለአምስተኛ ጊዜ በተለያዩ ኹነቶች ለአንድ ወር ያክል እያከበረ መኾኑን ተናግረዋል።

የባሕርዳር ዲስትሪክት ቀደም ሲል በደም ልገሳ፣ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በሚያግዙ ጥያቄ እና መልስ ውድድሮች እና በግንዛቤ ፈጠራ መድረኮች የሴቶችን ቀን ሲያከብር መቆየቱን አንስተዋል።

ዛሬ ደግሞ የሴቶችን የማደግ ራዕይ የሚያሳይ ንግድ እና የተሻለ እንቅስቃሴ ላላቸው ሴት ሥራ ፈጣሪዎች 25 ሚሊዮን ብር ለብድር በጀት መመደቡን ጠቅሰዋል። ለ50 ሥራ ፈጣሪዎችም ያለምንም ማስያዣ በዝቅተኛ ወለድ ለእያንዳንዳቸው የ500ሺህ ብር ብድር ማመቻቸቱንም ገልጸዋል።

ከማርች 8 ጀምሮም “አደይ እና ዛራ እችላለሁ” በሚል የሽያጭ ዘመቻ መካሄዱን አንስተዋል። ከዚህ በፊት ደንበኛ የነበሩ እና በዚህ አንድ ወር ውስጥ ከ500 ብር ጀምሮ ተጨማሪ ገንዘብ ለሚያስቀምጡ፣ ከ500 ብር ጀምሮ አዲስ የባንክ አካውንት ለሚከፍቱ እና በዲጂታል አማራጭ ክፍያ ለሚፈጽሙ ደንበኞች የሽልማት ኩፖን እየተሰጠ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

ወሩ ሲያልቅ ደግሞ ለአሸናፊው አንድ የ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ተሽከርካሪ ሽልማት ተዘጋጅቷል ብለዋል። ከዚህ ባሻገር ማንኛውም ሴት ቲክቶከር የሚሳተፍበት ሽልማት ማዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

ሴት ቲክቶከሮች ባላቸው ገጽ ባንኩን በማስተዋወቅ የተሻለ ተከታይ ላፈሩትም እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስ ሽልማት ማዘጋጀቱንም አንስተዋል። የዛሬው ኹነት በባሕር ዳር፣ በጅማ፣ በሃዋሳ እና በደሴ መከናወኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም እስከ መጋቢት 20/2018 ዓ.ም ሁሉንም ወጭ ሸፍኖ የሽያጭ እና የገበያ አማራጭ እንዲያገኙ እና ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ ይደረጋል ብለዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የሴቶችን ቀን ለተከታታይ በከተማዋ ሲከበር መቆየቱን ተናግረዋል። አቢሲኒያ ባንክ በተለያዩ ኹነቶች የሴቶችን ቀን በከተማዋ ማክበሩንም ገልጸዋል። ባንኩ ቀደም ሲል በተለያየ መንገድ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን እና ዛሬም አጋርነቱን በማሳየት ለሌሎች ተሞክሮ በሚኾን መንገድ ማክበሩንም አንስተዋል።

ሌሎች ባንኮችም ባደገ መንገድ ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በዛሬው ኹነት ተሳታፊ የኾኑ ነጋዴ ሴቶች አቢሲኒያ ባንክ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ዕድሎች መፍጠሩን ተናግረዋል። ለአብነትም በባሕርዳር ከተማ ለአምስት ቀን የሚቆይ ባዛር በማዘጋጀት ያለምንም ወጭ ለሸማቾች ምርት ለማስተዋወቅ እና ለመሸጥ እንዳመቻቸላቸው አንስተዋል።

ከዚህ ባሻገርም በአነስተኛ ወለድ በአምስት ዓመት የሚከፈል የብድር አገልግሎት እንደተመቻቸም ገልጸዋል። ሥራ ፈጣሪ ሴት ነጋዴዎች የእንዲህ ዓይነት ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ ሌሎች ተቋማትም እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአምስተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ ሊሰጥ ነው።
Next articleአማራ ባንክ እና ቪዛ ኩባንያ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን ስልታዊ አጋርነት መሠረቱ።