አምስተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ ሊሰጥ ነው።

10
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አምስተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እ.አ.አ በ2025 በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች የፖሊዮ በሽታ ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል። ለወረርሽኙ ምላሽ ለመስጠት የክትባት ዘመቻ እየተካሄደ መቆየቱንም ገልጸዋል።
የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል እና ለማጥፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው አምስተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከመጋቢት 18/2018 ዓ.ም እስከ መጋቢት 21/2018 ዓ.ም ድረስ ይሰጣል ብለዋል። በአማራ ክልልም ዘመቻው በተመሳሳይ ጊዜ ይካሄዳል ነው ያሉት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረገው ጥረት በሽታው እየጠፋ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትም ክትባት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም በሽታውን ለማጥፋት ጥረት እያደረገች ነው፤ ክትባቱ በተከታታይ በዘመቻ እየተሰጠ ያለውም ለዚህ እንደኾነ ነው የገለጹት።
በአማራ ክልል ከዚህ በፊት በተካሄዱ ዘመቻዎች በተወሰኑ አካባቢዎች ከ5 ዓመት እና ከ10 ዓመት በታች የኾኑ ከ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ተከትበዋል ብለዋል።
በአምስተኛው ዙር ዘመቻ በክልሉ 10 ዞኖች እና በአራት ከተማ አሥተዳደሮች ክትባቱ እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት። በእነዚህ አካባቢዎች ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የኾኑ ሁሉም ሕጻናት ክትባቱን ያገኛሉ ነው ያሉት። ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት በዘመቻው ይከተባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።
ለዘመቻው ከ12 ሺህ በላይ ክትባት ሰጭዎች፤ ከ4 ሺህ በላይ የክትባት ቡድኖች ይሰማራሉ ያሉት ዳይሬክተሩ የተለያዩ አካላት በኀላፊነት ዘመቻውን ይመራሉ ነው ያሉት። ክትባቱ ቤት ለቤት፣ በትምህርት ቤቶች እና በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
በዘመቻው የሚኖሩ ተግዳሮቶች መለየታቸውንም ገልጸዋል። የመንግሥት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሕጻናት ቤተሰቦች እና የሚመለከታቸው ሁሉ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል። አንድም ሕጻን ክትባቱን ሳያገኝ እንዳይቀር ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የትራንስፖርት እና የንግድ ተቋማት በየደረጃው የሚገኙ ጽሕፈት ቤቶች የክትባት ግብዓቶችን እስከሚፈለግበት ቦታ እንዲያደርሱም ጠይቀዋል። የጸጥታ አካላትም ትብብር እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።
ታላሚ የተደረጉ ሕጻናት በሙሉ ክትባቱን መውሰድ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየነዳጅ እጥረት እንዳይፈጠር አዲስ ስምሪት ተሰጥቷል።
Next articleአቢሲኒያ ባንክ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።