
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ሊያጋጥም ይችላል በሚል ሀገራት የየራሳቸውን መፍትሄ እየወሰዱ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም ከችግሩ ጋር ተያይዞ የነዳጅ እጥረት እንዳይገጥም ዜጎቿ ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀሙ አሳስባለች። የአማራ ክልልም ነዳጅን ዜጎች በቁጠባ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በክልሉ የነዳጅ እጥረት እንዳይፈጠር ነዳጅን በቁጠባ እና በጥንቃቄ ለመምራት የሚያስችል አዲስ ስምሪት ተሰጥቷል ብለዋል።
በዚህም መሠረት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚስተዋልባቸው ከተሞች ተለይተው ቅድሚያ እንዲያገኙ እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ሀገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችም ከመነሻቸው ጀምሮ ባሉ ማደያዎች በቅብብሎሽ ነዳጅ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ቁጠባውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በመንግሥት መስሪያ ቤት የሚገኙ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴያቸውን በሰዓት እንዲገድቡ እና የተሽከርካሪ ስምሪት መጠን እንዲቀንሱ አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈም በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር በተደረገ ክትትል፣ ከፋብሪካ ውጭ የነዳጅ ታንከር (ሳልቫቲዮ) የገጠሙ 26 ተሽከርካሪዎች እና አሽከርካሪዎቻቸው በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል ነው ያሉት። በተመሳሳይ መንግሥት ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጭ ስርጭት ሲያካሂዱ እና ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ ሲሸጡ በተገኙ ሦሥት የነዳጅ ማደያዎች ላይ የአንድ ዓመት እግድ መጣሉንም ገልጸዋል፡፡
የነዳጅ ስርጭቱን ፍትሐዊ ለማድረግ እና ብክነትን ለመከላከል በሚከናወነው የቁጥጥር ሥራ መመሪያ ተላልፈው የተገኙ 47 የንግድ ባለሙያዎች እና የሕግ አካላት ተጠያቂ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የቁጥጥር ሥራው በሁሉም ቦታዎች ወጥነት እንደሚጎድለው ነው የጠቆሙት፡፡ በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመቆጣጠር እና ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመግታት የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
