
ባሕር ዳር: መጋቢት16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጎግል በአንድሮይድ ስልኮች ላይ ካልታወቁ ምንጮች የሚጫኑ መተግበሪያዎችን (Sideloading) ለመቆጣጠር እንዲያስችለው የ24 ሰዓት የቆይታ ጊዜን የሚያስገድድ አዲስ አሠራር አበጅቷል።
“አድቫንስድ ፎሎው (Advanced Flow)” የተሰኘው ይህ አሠራር ተጠቃሚዎች በአጭበርባሪዎች ተገፋፍተውና ተቻኩለው አደገኛ መተግበሪያዎችን በመጫን ለግል መረጃ ስርቆት እንዳይጋለጡ ለማድረግ ያለመ እንደኾነ ጎግል ገልጿል።
ይህ ጥብቅ ቁጥጥር ያስፈለገው “Perseus” የተሰኘ አዲስ እና አደገኛ ቫይረስ እንዲኹም ሌሎች 17 የሚኾኑ የማልዌር ዝርያዎች በዓለም ዙሪያ የሰዎችን የባንክ መረጃና የዲጂታል ማንነት እየዘረፉ በመኾኑ ነው ይላል የኢንሳ መረጃ።
ጎግል በዚህ አሠራር የፕሌይ ፕሮቴክ (Play Protect) የደህንነት መጠበቂያን በማጠናከር የተጠቃሚዎችን ስልክ ከአደጋ ለመታደግ በማቀድ ነው።
እንደ ጎግል ገለጻ አዲሱ መመሪያ ተፈጻሚ የሚኾነው ማንነታቸው በጎግል ያልተረጋገጠ አልሚዎች (Unverified Developers) ለሚያበለጽጓቸው መተግበሪያች ብቻ ነው። ተጠቃሚዎች እነዚህን መተግበሪያዎች ለመጫን ዴቨሎፐር ሞድን ማብራት፣ ስልካቸውን በድጋሚ ማስጀመር (Restart) እና ለ24 ሰዓት በትዕግስት መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
ይህም በአጥቂዎችና በተጠቃሚች መካከል የጊዜ ልዩነት በመፍጠር ጥቃቱን ለመቀነስ ይረዳል። ይህ የጎግል ውሳኔ ከተለያዩ የመተግበሪያ አልሚዎች እና የዲጂታል መብት ተሟጋቾች ትችት እየቀረበበት ይገኛል።
ነገር ግን ተቺዎቹ አሠራሩ የግል ነፃነትን የሚገድብ፣ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለክትትል አሳልፎ የሚሰጥና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ እንቅፋት የሚፈጥር “የቢሮክራሲ አጥር” ነው በማለት እየተቃወሙት ይገኛሉ።
ይህ የጎግል ውሳኔ እንደ ኢትዮጵያ የዲጂታል ባንኪንግና የሞባይል ገንዘብ (እንደ ቴሌብር) ዝውውር በከፍተኛ ኹኔታ እያደገ በመጣባቸው ሀገራት ከሳይበር ጥቃት ለመታደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ተጠቃሚዎች ስለ ቴክኖሎጂ ደህንነት ያላቸው ግንዛቤ ገና በማደግ ላይ ባለበት ኹኔታ፣ እንዲህ ያለው የጥበቃ ጊዜ በአጭበርባሪዎች ተታለው ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ እንዳይዳረጉ ጠንካራ መከላከያ ኾኖ ያገለግላል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
