
አዲስ አበባ: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እና የጣሊያን የመሠረተ ልማት እና የከተማ መልሶ ግንባታ ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።
በግንባታ መስክ በኤሌክትሪክ እና በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ማምረት የተሠማሩ ድርጅቶች፤ የፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎችም በፎረሙ ላይ ተሳትፈዋል።
በኢትዮጵያ በግንባታው ዘርፍ ለረጅም ዓመታት በመሠማራት የሚታወቀው በቀድሞው ስሙ ሳሊኒ አሁን ላይ ዊቢውልድ ተብሎ የሚጠራው ድርጅት በፎረሙ ተሳትፏል።
በፎረሙ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ መንግሥት እየተከተለው ባለው የብዝኃ ኢኮኖሚ በርካታ የውጭ ሀገራት ድርጅቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ፈሰስ እንዲያደርጉ እያስቻለ መኾኑን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማው ለማልማት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ሀገራት ድርጅቶችን ለመቀበል ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የጣሊያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለማቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ማሪያ ትሪፖዲ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ሀገራት ድርጅቶች ገብተው እንዲያለሙ ባመቻቸው ዕድል መሠረት የጣሊያን ድርጅቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
