
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ከተለያዩ ቀበሌዎች ከተውጣጡ አርሶ አደሮች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና የጸጥታ ሥራዎች ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ፕላን እና ልማት መምሪያ ኀላፊ መኩሪያው ገረመው ሀገር እና ሕዝብን ለጸጥታ ችግር የሚዳርጉ የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ሴራ በውል በመገንዘብ ማኅበረሰቡ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አንስተዋል።
በቋሪት ወረዳ ውስጥ በሕዝብ ዘንድ በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን መንግሥት ፈጣን ምላሽ እየሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል። ሕዝቡ ከልማቱ ጎን እንዲሰለፍም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የቋሪት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መኳንንት ወርቅነህ የወረዳው ሕዝብ ላለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ላልተፈለገ ስቃይ እና እንግልት እንዲዳረግ ምክንያት የኾኑ ጸረ ሰላም ኃይሎችን በቃ ማለት ይገባል ብለዋል።
መንግሥት የሕዝቡን የልማት ፍላጎት እውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደኾነም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ በቀጣይ ለአርሶ አደሮች የሚቀርቡ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቶችን ለታለመው ዓላማ ብቻ እንዲጠቀሙ እና ለሰላም ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት መንግሥት ጠንከር ያለ የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲሠራላቸው ጥሪ አቅርበዋል። “ጦርነት ሰልችቶናል፤ ሰላም እና ልማት ናፍቆናል” በማለት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በመድረኩ ማስተጋባታቸውንም ከቋሪት ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
