በኑሮ ውድነት ላይ ሕገ ወጥ የታሪፍ ጭማሪ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው።

13
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ሃብታሙ አሰማ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። የእግር አካል ጉዳት ያለባቸው አቶ ሃብታሙ ስምንት የቤተሰብ አባላት እንዳሏቸው ገልጸውልናል። አነስተኛ የፍጆታ ምርቶችን እየነገዱ ቤተሰባቸውን እንደሚያሥተዳድሩም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ወደ ሥራ ቦታቸው ለመጓዝ የአካል ጉዳተኛ ሞተር ሳይክላቸውን ይጠቀሙ ነበር። አሁን ላይ ግን የቤንዚን ዋጋ ከአቅማቸው በላይ በመኾኑ ታክሲ ለመጠቀም ተገድደዋል። እንዲያም ኾኖ ሥራ ቦታ ለመድረስ ሁለት ታክሲ መያዝ ግድ ስለሚላቸው በቀን ከ 160 ብር ያላነሰ ለታክሲ እንደሚከፍሉ ነው የነገሩን።
ከትራንስፖርት ወጭው በተጨማሪ ጠዋት እና ማታ የታክሲ ወረፋ መጠበቁም ሌላ ፈተና እንደኾነባቸው ገልጸዋል። ወቅቱ የንግድ ሥራ የተቀዛቀዘበት እና የኑሮ ውድነት ያለበት ነው ያሉት ባለታሪካችን የትራንስፖርት ዋጋ መናር ሲጨመር ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይኾን ሰጋት አለን ብለዋል።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ በከተማዋ ዋና ዋና ፌርማታዎች ባደረገው ቅኝትም ታክሲዎች እና ባጃጆች በትንሹ ከ5 ብር ጀምሮ የዋጋ ጭማሪዎችን እንዳደረጉ ተመልክቷል። በየፌርማታው ረጃጅም የነዋሪዎች ሰልፍ እና ረጅም ሰዓት ታክሲ የሚጠብቁ ሰዎችንም ተመልክተናል። ይህም በተለይ በየቀኑ የሕዝብ ተሽከርካሪዎችን የሚጠቀሙ፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን እና መሰል ነዋሪዎችን እያማረረ ይገኛል።
አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ያነጋገርናቸው የታክሲ እና የባጃጅ አሽከርካሪዎች ማደያዎች ላይ ረጅም ወረፋዎችን በመጠበቅም ቢኾን ነዳጅ እያገኘን ነው ብለዋል። ነገር ግን በወረፋ ከሥራ ውጭ የሚኾኑበት ቀን ስለሚበዛ እና አልፎ አልፎም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ስለሚጠቀሙ በመደበኛ ታሪፍ መሥራት አዋጭ አይደለም ብለዋል። በዚህ ምክንያት ዋጋ እንጨምራለን ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አደራ ጋሼ ዓለም አቀፍ ችግሩ በፈጠረው ጫና ምክንያት የነዳጅ አቅርቦት እንደበፊቱ አለመኾኑን
ጠቅሰዋል። ያለውን ነዳጅ በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። የተቀዳላቸውን ነዳጅ በጥቁር ገበያ እየሸጡ ማደያ በየቀኑ ያለአግባብ የሚሰለፉ እንዳሉም ጠቁመዋል። ታክሲ፣ ዳማስ እና ባጃጆች የቀዱትን ነዳጅ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት።
ነዳጅ ከማደያ ያወጣውም፣ ያላወጣውም “ነዳጅ በጥቁር ገበያ ነው የገዛነው እያለ” ሕገ ወጥ ታሪፍ በማኅበረሰቡ ላይ እየጫነ በመኾኑ ጥብቅ ቁጥጥር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ ትራንስፖርት የስምሪት አቅርቦት ብቃት ማረጋገጫ አሥተባባሪ ደመላሽ ዘውዱ በከተማዋ አሽከርካሪዎች የቀዱትን ነዳጅ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማድረግ አዲሰ አሠራር መጀመሩን ጠቁመዋል።
ቤንዚን እና ናፍጣ ሲሸጡ የተገኙ አሽከርካሪዎች ከ3 ሺህ ብር ጀምሮ ቅጣት፣ ከመስመር የማገድ እና ናፍጣ እንዳይቀዱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በቅርቡም የቀዱትን ነዳጅ በአግባቡ ያልተጠቀሙ እና መስመር ያልሸፈኑ 11 ታክሲዎች ተቀጥተዋል ብለዋል።
ጠዋት እና ማታ የሚታየውን የትራንስፖርት ተጠቃሚ ሰልፍ ለማስቀረት የኤሌክትሪክ አውቶብሶች እንደ መፍትሔ እየተወሰዱ መኾናቸውን ገልጸዋል። የብዝኃ ትራንስፖርትን በማስፋፋት እና ከነዳጅ ጥገኝነት በመራቅ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባም ነው ያነሱት።
የባሕር ዳር ከተማ መንገድ ትራንስፖርት የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ቡድን መሪ ብርሃኔ አበበ ሕገ ወጥ የታሪፍ ጭማሪውን ለመቆጣጠር አራት ቡድን ተቋቁሞ በሁሉም አቅጣጫዎች ሁሉንም የትራንስፖርት ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።
ሕገ ወጥ ጭማሪ ያደረጉትን እየቀጣን ነው ብለዋል። ጭማሪ ካላደረጋችሁ አንጭንም የሚሉም እየተያዙ እና እየተቀጡ መኾናቸውን ገልጸዋል። ሕገ ወጥ ታሪፉን ለመቆጣጠር ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ እየተፈጠረ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምርጫ ብሔራዊ ጥቅምን እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ሊኾን ይገባል።
Next articleነዳጅን በቁጠባ እና በአግባቡ እየተጠቀምን ነው።