
አዲስ አበባ: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከሦስት ወራት በፊት የማስፋፊያ ሥራው የተጀመረው የእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ የግንባታ ሥራው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡
የእንዶዴ ደረቅ ወደብ አጠቃላይ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር ሙባረክ መገርሳ ወደቡ በውስጡ አምስት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መያዙን ገልጸዋል።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በዋናነት የኮንቴነር ጭነቶች የመያዝ አቅምን ማሳደግ፤ እንደ ማዳበሪያ ያሉ ብትን ጭነቶች የሚራገፉበት የባቡር መስመር ዝርጋታ እና ጭነቶችን ለማራገፍ ይወስድ የነበረውን የጊዜ መጓተት ለማስቀረት ታልሞ እየተገነባ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ከዚህ ቀደም 1ሺህ ኮንቴነሮችን ብቻ ይይዝ የነበረውን የወደቡን የጭነት አቅም ወደ 4 ሺህ 300 የጭነት ኮንቴነሮች እንዲይዝ ተደርጎ ተገንብቷል ነው ያሉት፡፡
በባቡር ተጭነው ከውጭ የሚገቡ እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በወደቡ ለማራገፍ ከ10 ሰዓት በላይ ይወስድ የነበረውን የጊዜ መጓተት በማስቀረት በ30 ደቂቃ ውስጥ ብቻ ባቡሮቹ ጭነታቸውን እንዲያራግፉ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ከዚህም ባነሰ የባቡር ትራንስፖርት ወጭ ፈጣን አገልግሎትን በወደቡ በመስጠት በአስመጭ እና ላኪዎች በኩል ይደርስ የነበረውን የጊዜ እና የውጭ ምንዛሬ ጫናን በማስቀረት ኢኮኖሚው ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡
ከመዲናዋ አዲስ አበባ በቅርብ እርቀት ላይ የተገነባው የእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም የሀገሪቱ የወጭ ገቢ ምርት ማሠራጫ ማዕከል በመኾን ኢኮኖሚውን እንደሚደግፍ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅም ቀን እና ማታ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
