
ባሕር ዳር (መጋቢት 16/2018 ዓ.ም) በአማራ ክልል የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርቶችን በማምረት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ ለወጣቶች አዲስ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ።
ይህ የኢንዱስትሪ ዕድገት ለዘመናት የቆየውን የመንግሥት ሥራ ብቻ የመጠበቅ ባሕል በመስበር፣ ወጣቶች በግል ዘርፉ ውስጥ ክህሎታቸውን አውጥተው እንዲያሳዩ እና የነገ ራዕያቸውን እንዲሰንቁ ምቹ መድረክ ፈጥሯል።
በዩኒሰን የኢንዱስትሪ ግሩፕ ውስጥ በሽያጭ ባለሙያነት የሚያገለግለው ወጣት ማንደፍሮ ገብረማርያም ከተመረቀ አንድ ዓመት በኋላ በጋርመንት ኢንዱስትሪዎች ተቀጥሮ ለሦሥት ዓመት ከስድስት ወር መሥራቱን አስታውሷል።
አሁን በተሰማራበት የኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሻለ ልምድ እና ግልጽ የኾነ የወደፊት ተስፋ ማግኘቱን ተናግሯል። አንደ ዩኒሰን ዘይት ፋብሪካ ያሉ ተቋማት የሥራ ልምድ ለሌላቸው አዲስ ተመራቂዎች በራቸውን ክፍት ማድረጋቸው ወጣቶች ከትንሽ ተነስተው በትልቅ የኀላፊነት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የሙያ መሰላል እየኾኑላቸው መኾኑን ገልጿል።
የእነዚህ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ውጤቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ብቻ የተገደበ እንዳልኾነም ተናግሯል። ፋብሪካዎቹ የሚያመርቷቸውን ምርቶች በቀጥታ ለገበያ ማቅረባቸው በውጭ እና በሀገር ውስጥ ምርቶች መካከል ያለውን የዋጋ ልዩነት በማጥበብ የሸማቹን ማኅበረሰብ የኑሮ ጫና በመቀነስ ረገድ የላቀ ፋይዳ እንዳላቸውም ጠቁሟል።
ምርቶቹ በቅናሽ ዋጋ ለሕዝቡ መቅረባቸው የገበያ መረጋጋትን ከመፍጠርም በላይ ለአካባቢው ነዋሪ ትልቅ የኢኮኖሚ እፎይታ ይሰጣል ነው ያለው።
የዩኒሰን ዘይት ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጅ ዳዊት ታረቀኝ ፋብሪካው ተኪ ምርት በማምረት ገበያ ከማረጋጋት እና የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባሻገር ለሥራ ዕድል ፈጠራም ትኩረት ሰጥቷል ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅት የዘይት ፋብሪካው ለብቻው ለ148 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አመላክተዋል።
ፋብሪካው በቀጣይ እየተስፋፋ ሲሄድ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል የአሁናዊ ቁጥሩን ከሦሥት እጥፍ በላይ ሊያሳድገው እንደሚችልም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አዲሴ መብራቴ ቢሮው በጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚታዩ መዋዠቆችን ለመቀነስ ትኩረቱን በቋሚ የሥራ ዕድል ላይ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም በአምራች ዘርፉ በተሰማሩ ባለሀብቶች አማካኝነት ለ30 ሺህ 209 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።
ይህ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ ለ16 ሺህ 303 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከተያዘው ዕቅድ አንጻር ሲታይ ከእጥፍ በላይ ስኬት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራው ጎን ለጎንም ቢሮው የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ለማድረግ በምርት ጥራት ማሻሻያ ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት። ይህም አምራች ኢንዱስትሪዎች ያላቸውን የማምረት አቅም በመጠቀም ለዜጎች ዘላቂ የገቢ ምንጭ ከመኾን ባለፈ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የራሳቸውን አዎንታዊ ድርሻ እንዲያበረክቱ የሚያስችል መኾኑም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
