
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ)በሀገር መከለካያ ሠራዊት የምሥራቅ እዝ በግዳጅ ላይ ለሚገኙ ለሠራዊቱ ክፍል መሪዎች የማዕረግ ዕድገት ሰጥቷል። መሪዎችም የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ ኀላፊ ጄኔራል ደስታ አብቸ ማዕረግ በቆይታና በጅምላ የሚሰጥ ሳይኾን የሕይወት መስዋዕትነትን ከፍለው የመቆያ ጊዚያቸውን ጨርሰው ፣ ሀገርን ሰላም አድርገው እና ለሰላም ከፍተኛ ዋጋ ከፍለው በሥራ ብልጫ ላሳዩ መሪዎች የሚሰጥ ክብር ነው ብለዋል።
ይህ ማዕረግ የመንግሥት እና የሕዝብ አደራ ያለው ፣ ከፍተኛ ተጠያቂነትና ኀላፊነት ጭምር ይዞ የሚመጣ መኾኑን ገልጸዋል።
የማዕረግ እድገት የተሰጣቸው መሪዎች የሀገር መከለካያ ሠራዊት ኀላፊነት እና ተጠያቂነት የሰጣቸው መኾኑን ተገንዝበው ለላቀ ግዳጅ እንዲነሱ አሳስበዋል።
ከአሁን በፊት ሲወጡት የነበረውን ግዳጅ በላቀ ብቃት እና ጀግንነት እንደሚወጡም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ለፍታችሁ ላገኛችሁት ማዕረግ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ምሥራቅ እዝ ጀግና መሪዎች የሚወጡበት ታሪካዊ የኾነ፣ የሀገር እና የሕዝብ ዋስትና፣ በጀግንነት መስዋዕትነት የከፈሉ እና መክፈል የሚችሉ የሕዝብ ልጆች የሚፈጠሩበት እዝ መኾኑን ተናግረዋል።
የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ ኀላፊ ጄኔራል ደስታ አብቸ እና ለሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች የባሕርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራዎችንም ጎብኝተዋል።
የጣና ዳር የመዝናኛ ሥፍራዎችን ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ፣ የከተማው ውበት የኾኑትን መንገዶችን፣ ድልድዮችን እና የባሕርዳር ስቴዲየምን ነው የጎበኙት።
ለጎብኝዎች ማብራሪያ የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተሻገር አዳሙ የጀግናው የምሥራቅ እዝ የሠራዊት አባላት የክልሉን ሕልውና ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ከምሥራቅ እዝ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በተገኘው ሰላም ባሕርዳር ከተማ የልማት ሥራዎችን ያለምንም የጸጥታ ስጋት እያከናወነች መኾኗን ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
