የተቋማት ነዳጅን በቁጠባ የመጠቀም ልምድ ምን ይመስላል?

6
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ በአንድ ማኅበረሰብ ወይም ሀገር እድገት ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ሚና አለው።
መንግሥታዊም ኾኑ የግል አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ውጤታማ አገልግሎት ሲሰጡ የዜጎችን ሕይወት ያቃልላሉ፤ አመኔታን ይገነባሉ፤ ለኢኮኖሚ እድገትም መሠረት ይሆናሉ። ይህን ሚና ለመወጣት ከሚያግዙ መሠረታዊ ግብዓቶች መካከል ነዳጅ አንዱ ነው።
በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረው ቀውስ ተከትሎ የነዳጅ እጥረት እንዳይከሰት ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም እንደሚገባ መንግሥት ማሳሰቡ ይታወሳል።
ይህ ካልኾነ ግን የመንግሥትም ኾነ የግል ተቋማትን የሚፈትን ነው። አንዳንዶቹ ተቋማት አሠራሮቻቸውን ቀደም ብለው ለማሻሻል ጥረት ማድረጋቸው ችግሩን ያቀልላቸዋል።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የአመልድ ኢትዮጵያ የንብረት እና አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አሥኪያጅ ተስፋሁን አያል የነዳጅ አጠቃቀምን ለማሻሻል እና የአየር ንብረት ጥበቃ ሥራ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ እንደ ተቋም የተለያዩ ተግባራት ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ተቋሙ ቀደም ሲል የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ላይ ይታዩ የነበሩ የነዳጅ አጠቃቀም ውስንነቶችን ለማሻሻል ለሁሉም ተሽከርካሪዎች የተሽከርካሪ መከታተያ መሣሪያ (GPS) መግጠሙን ገልጸዋል። በዚህም አንድ ተሽከርካሪ በአንድ ወር እስከ 200 ሊትር ነዳጅ ይጠቀም የነበረውን ወደ 40 ሊትር ዝቅ እንዲል እንዳስቻለም ጠቅሰዋል።
የተሽከርካሪ መከታተያ መሣሪያ የተሽከርካሪዎችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ከመቆጣጠር ባሻገር የነዳጅ ሃብትን መቆጠብ አስችሎናል ብለዋል።
አሁን ላይ ለተፈጠረው የነዳጅ እጥረት እንዲህ ዓይነት አሠራሮችን መከተል አዋጪ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትራንስፖርት ስምሪት አገልግሎት ኀላፊ ሀብታሙ ተስፋዬ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ተሽከርካሪዎችን ለሥራ የሚጠቀም በመኾኑ ቀደም ሲል የነዳጅ አጠቃቀም ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶች እንደነበሩ አንስተዋል።
ችግሩን ለማሻሻልም የተሽከርካሪ መከታተያ መሣሪያ መተግበር የጀመሩ ተቋማት ላይ ልምድ በመውሰድ ወደ ተግባር ለመግባት ተቋሙ እንቅስቃሴ ሲያደረግ እንደነበር ተናግረዋል።
በሌላ በኩል አሁን ላይ ከተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ከመፈጠሩ አስቀድሞ ዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አገልግሎት መጀመሩን እና ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት የመጠቀም እሳቤ እንደነበረው ገልጸዋል። በዚህም ሁለት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ነው የጠቀሱት።
ነዳጅ ካለው ዋጋ እና አቅርቦት አኳያ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም አዋጪ እንዳልኾነም ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቀጣይ አቅጣጫ እና ፍላጎት አጠቃላይ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር እንደኾነም ጠቅሰዋል። ለዚህም የዩኒቨርሲቲው ኢንተርፕራይዝ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ገዝቶ ለተቋሙ እንዲያከራይ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደኾነ ነው የጠቆሙት።
ወቅታዊ ችግሮችን ለማለፍ ነዳጅን በቁጠባ እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ጎንደር ከተማዋ ብቻ ሳይኾን ገጠሩም በኮሪደር ልማት አዲስ የታሪክና የሥልጣኔ ምዕራፍ ተከፍቶለታል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article“ምሥራቅ እዝ ጀግና የሕዝብ ልጆች የሚፈጠሩበት ነው” ጄኔራል ደስታ አብቸ