
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሳይና ሳቢያ የገጠር ቀበሌ የተገነቡ የገጠር ኮሪደር ሞዴል ቤቶችን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጎንደር ከተማዋ ብቻ ሳይኾን ገጠሩም በኮሪደር ልማት አዲስ የታሪክና የሥልጣኔ ምዕራፍ ተከፍቶለታል ብለዋል።
በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሳይና ሳቢያ የገጠር ቀበሌ የተገነቡ የገጠር ኮሪደር ሞዴል ቤቶችን መርቀን ለአገልግሎት አብቅተናል። ይህ ፕሮጀክት ከተማዋን ብቻ ሳይኾን ገጠሩንም እኩል የማዘመን፣ የማስዋብና በልማት የማሸጋገር ሀገራዊ ራዕይ በተግባር የታየበት መኾኑን ገልጸዋል።
በአንድ ወር የግንባታ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀው ይህ ሞዴል መንደር በአካባቢው ለረጅም ዓመታት የቆየውን የጤና ጣቢያ፣ የመብራት እና የውኃ አገልግሎት ጥያቄ በተግባር መልሷል ነው ያሉት።
የአካባቢውን ቁሳቁስ ከዘመናዊ መሃንዲስ ዕውቀት በማሰናሰል በአካባቢው በሚታወቀው የ”ደቢያት” የትብብር ባሕል ደግሞ አርሶ አደሮችን ቀጥታ በማሳተፍ ዘመናዊ ቤቶች ተገንብተዋል። የሰዎች መኖሪያን ከእንስሳት መጠለያ በመለየት ለጤናማና ለሥልጡን አኗኗር መሠረት ጥለናል ብለዋል።
ዙሪያውን በተቀናጀ የሌማት ትሩፋት የታጀበው ይህ የገጠር ኮሪደር፣ አርሶ አደሮችን የዘመናዊነት እና የምርታማነት ባለቤት የሚያደርግ ነው።
ዛሬ ጎንደርም ኾነች ድፍን ሀገራችን ከተማው ብቻ ሳይኾን ገጠሩም እኩል እየተዋበ፣ በልማት እየተገነባ እና በዕድገት ፍኖት ላይ በጽኑ መሠረት እየተራመደ ይገኛል። ይህ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የማሸጋገር ትልቁ ማሳያችን ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
