“ዘመናዊ ኑሮ ልንኖር ነው” የገጠር ኮሪደር ተጠቃሚ አርሶ አደሮች

21
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የገጠር ኮሪደር ልማት የገጠር መንደሮችን ከመሠረተ ልማት ጋር በማስተሳሰር የማልማት ስልት ነው። ይህ የልማት ስልት የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ የትምህርት እና የጤና አቅርቦቶችን በአንድ አካባቢ አስተሳስሮ በማሟላት የገጠሩን ማኅበረሰብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያለመ ነው።
በአማራ ክልል የገጠር ኮሪደር ተግባራዊ ከተደረገባቸው አካባቢዎች መካከል የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የገጠር ቀበሌዎች ይገኙበታል። በከተማ አሥተዳደሩ የገጠር ቀበሌ በኾነችው የሳይና ሳብያ ቀበሌ የገጠር ኮሪደር ልማት ተሠርቷል።
የልማቱ ተጠቃሚ የኾኑት አርሶ አደር ደሴ ሲሳይ የጤና ተቋማት እጥረትን ጨምሮ አካባቢው በችግር ውስጥ መኖራቸውን ያስታውሳሉ። የኮሪደር ልማት በከተማ እንጂ በገጠር ሰምቼው አላውቅም ነበር የሚሉት አርሶ አደሩ መንግሥት በቅርቡ በጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት ተጠቃሚ በመኾኔ ተደስቻለሁ ብለዋል።
“የተሠራው ቤት ሎጅ እንጂ የግለሰብ ቤት አይመስለኝም” በማለት ያላቸውን ስሜት ገልጸውልናል። አርሶ አደር ነኝ አርሳለሁ፤ አትክልት እተክላለሁ፤ ከብቶችንም አረባለሁ ያሉት አቶ ደሴ በገጠር ኮሪደር የተሠራው ቤት እነዚህን ሁሉ በልዩ ሁኔታ በመሥራት የተሻለ ኑሮ ለመኖር የሚያስችል መኾኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር ዩሐንስ ባዜ በኮሪደር ልማቱ የተሻለ ኑሮ ለመኖር አዲስ ተስፋ ሰጥቶናል ብለዋል። ልማቱ ከአሁን በፊት ይኖሩት ከነበረው ዘልማዳዊ አኗኗር ወደ ዘመናዊ አኗኗር የሚያሸጋግር እንደኾነ ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ ያመጣላቸውን አዲስ ተስፋም “እኛም በገጠር ዘመናዊ ኑሮ ልንኖር ነው” በማለት አርሶ አደሮች ገልጸዋል። ሁሉም አካባቢ እንደዚህ ቢሠራ የተሻለ ኑሮ እንደሚኖር ተናግረዋል።
የተሠራውን የገጠር ኮሪደር ልማት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልል እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ጎብኝተውታል ።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የመገጭ ግድብ ፕሮጄክትን ጎበኙ።
Next article“ጎንደር ከተማዋ ብቻ ሳይኾን ገጠሩም በኮሪደር ልማት አዲስ የታሪክና የሥልጣኔ ምዕራፍ ተከፍቶለታል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ