የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤት ዳኞች ምርጫ ማካሄዱን አስታወቀ።

11

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የተካሄደውን የባሕል ፍርድ ቤት የዳኞች ምርጫን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የአማራ ክልል ምክር ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና ዕውቅና ለመስጠት የሚያስችል አዋጅ ቁጥር 298/2017 መውጣቱን አስታውሰዋል።

አዋጁን ተከትሎ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኙ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች ላይ ጥልቅ ጥናቶችን ማካሄዱን ገልጸዋል።

15 የሚኾኑ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች መለየታቸውን እና ዕውቅና እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

በጥናቱ መሠረት በተዘጋጀው ዝርዝር የአተገባባር መመሪያ መሠረት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከጥር 26/2018 እስከ የካቲት 30/2018 ድረስ የመጀመሪያው ዙር የባሕል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች ምርጫ መካሄዱንም አስታውቀዋል።

በተካሄደው ምርጫ በ1 ሺህ 149 ቀበሌዎች 5 ሺህ 494 የባሕል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች ተመርጠዋል፤ ከነዚህ መካከልም 437 ዳኞች ሴቶች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

ቀደም ሲል በዘርፉ ሲካሄዱ የነበሩ ጥናቶች ሴቶች በሽምግልና ሥርዓት ተሳትፎ እንደሌላቸው ተደርጎ ይታሰብ የነበረውን እሳቤ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ እና በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ሴቶች የተመረጡበት፤ ተሳትፎ ያደረጉበት እና ሴቶች አለመግባባቶችን ለመፍታት ሚና እንዳላቸው የታየበት መኾኑን ገልጸዋል።

በምርጫ ሂደቱ ማኅበረሰቡ በመውጣት በባሕሉ እና በወጉ መሠረት ሊዳኙ የሚችሉ ሥነ ምግባር ያላቸው ቅቡል እና የሚታመኑ የባሕል ፍርድ ቤቶች ዳኞችን መምረጡን ተናግረዋል።

በሂደቱ የወረዳ ፍርድ ቤቶች ዳኞች፤ የባሕል እና ቱሪዝም ባለሞያዎች አስቸጋሪ ቦታዎች ድረስ በመሄድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርጫውን በስኬት በማካሄዳቸውም አመስግነዋል።

በቀጣይ ለተመረጡ የባሕል ሽምግልና ፍርድ ቤት ዳኞች ሥልጠና ይሰጣል ነው ያሉት። በቀሪ ቀበሌዎች ደግሞ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዙር ምርጫዎች ይካሄዳሉ ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየምስሎችን እውነት መኾን አለመኾን እንዴት እናጣራ?
Next articleበሐረሪ ክልል ነዳጅን በሕገ ወጥ መንገድ ሲሸጡ በተገኙ ማደያዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ።