
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመካከለኛው ምሥራቅ የተነሳው ግጭት የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል። ነዳጅን ገዝተው ለሚጠቀሙ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ደግሞ የነዳጅ እጥረቱ በማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ይህንን ፈተና ለመሻገር የኢትዮጵያ መንግሥት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም እንደሚገባ አሳስቧል።
በነዳጅ እጥረት ምክንያት ዜጎች እንዳይነገላቱ የግል እና የመንግሥት አሽከርካሪዎች እገረ መንገዳቸውን ወደ ሚሄዱበት ቦታ በመልካም ትብብር ማኅበረሰቡን እየተባበሩ መኾኑን ታዝበናል።
በተቃራኒው ደግሞ የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች የነዳጅ እጥረቱን ምክንያት በማድረግ ከነበረው የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ በማድረግ ማኅበረሰቡን ለእንግልት እየዳረጉ መኾኑን በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ተጨማሪ ክፍያ ለመክፈል መገደዳቸውን ነግረውናል። መንግሥት ነዳጅ ቆጥባችሁ ተጠቀሙ አለ እንጂ ያለአግባብ የትራንስፖርት ታሪፍ ጨምሩ አላለም የሚሉት ነዋሪዎቹ ይህን ጊዜ በመተባባር እና በመተዛዘን መሻገር ይጠይቃልም ብለዋል። መንግሥትም ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ሕገ ወጥ ጭማሪ በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮችን እያስከተለ መኾኑን ገልጸዋል። በአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ቢሮ የመንገድ ደኅንነት ትራንስፖርት ክትትል እና ቁጥጥር ዳይሬክተር ደሳለኝ አዳነ የነዳጅ እጥረትን ምክንያት በማድረግ የሚደረግ የታሪፍ ጭማሪ እና የትርፍ መጫንን ለመከላከል በክልሉ ስምንት ሪጅኦ ፓሊታንት ከተሞች ስምሪት ተደርጎ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘርፉ በየጊዜው ቁጥጥር የሚፈልግ መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ47ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር ተደርጎ
2ሺህ 630 ተሽከርካሪዎች ጥፋተኛ ኾነው በመገኘታቸው በገንዘብ መቀጣታቸውን አስረድተዋል።
በተለይም ትርፍ በመጫን 554 እና ከታሪፍ በላይ በማስከፈል ደግሞ በ343 አሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።
በክልሉ ባለፋት ስምንት ወራትም ትርፍ በመጫን ከ24ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ጥፋተኛ ኾነው በመገኘት ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ መቀጣታቸውን አስታውሰዋል። ከታሪፍ በላይ በማስከፈል ደግሞ ከ19ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ቅጣት መቀጣታቸውን ተናግረዋል።
የትራንስፖርት ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። ማኅበረሰቡም ሕገ ወጥ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ሲመለከት ለትራፊክ እና ለትራንስፖርት ቁጥጥር አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራው ድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
