
ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ለክልሉ የሕዝብ ግንኙነት መሪዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡
በሥልጠና ማስጀመሪያ መርሐግብሩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ ኮርፖሬሽኑ ከባሕላዊ አሠራር ወደ ዘመናዊ የዲጂታል ሚዲያ ሽግግር እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
መደበኛው ሚዲያ ከዲጂታል መድረኮች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ያለበት ጊዜ ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
አሚኮ ለክልሉ ሕዝብ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ነው፤ ይህንንም አጠናክሮ ለመቀጠል በዲጂታል መድረኮች ላይ የተቀናጀ አቅም የመፍጠር ግብ ያለው መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ጥራት ያለው እና ፈጣን መረጃ ለሕዝብ ለማድረስ በጋራ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በተቋማት ግንኙነት እና በመረጃ ፍስሰት ረገድም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሎች ለሚዲያ ተቋማት ዋነኛ የመረጃ ምንጭ መኾን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉን ማዘመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መኾኑን ተረድቶ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥትም ኾነ ግለሰቦች መረጃን በማግኘት እና በመስጠት በኩል ቀዳሚ መኾን ካልተቻለ ታላሚ ሥራዎችን ለማሳለጥ እንደሚቸግር ገልጸዋል፡፡ ሚዛናዊ መረጃዎችን ለሕዝብ በማድረስ ተቋማት እንዲጠናከሩ እና የሚሠሩት ሥራ ለሕዝብ ግልጽ እንዲኾን ማድረግ የዘርፉ መሪዎች ትልቅ ኀላፊነት መኾኑንም አስገንዝበዋል።
እውነተኛ እና ተዓማኒ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን ማሰራጨትና መቀበል እንደሚገባም ጠቁመዋል። በዚህ ረገድ ውስንነቶች እንደሚስተዋሉ ጠቅሰው ክፍተቱን በዕውቀት እና በክህሎት መሙላት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
“አሚኮ ተዓማኒነት እና ፋይዳ ያላቸውን የዲጂታል ሚዲያ መረጃዎች እና መልዕክቶች በማስተላለፍ ሕዝብን እያገለገለ ነው፤ እንዲህ አይነት የተጣሩ መልእክቶችን የማሰራጨት ልምድ ሊዳብር ይገባል” ብለዋል። እውነተኛ መረጃዎች በተገቢው ሰዓት ለሕዝብ መድረስ ካልቻሉ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎች የበላይነት ሊይዙ ስለሚችሉ ባለሙያዎች በዕውቀት ላይ ተመሥርተው መረጃን ሸድሞ የማድረስ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አሚኮ ከ30 ዓመታት በላይ ያለውን የዳበረ የሚዲያ ተሞክሮ ለኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ለማጋራት መድረኩ የተሻለ አማራጭ መኾኑን አቶ ዓባይ ጠቅሰዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
